በሴካፋ ከ15 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከምድቡ ማለፍ አልቻለም

76
ነሀሴ 16/2011 በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) ከ15 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከምድቡ ማለፍ አልቻለም። በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) አማካኝነት የተዘጋጀው ከ15 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ከነሐሴ 10 ቀን 2011 ዓ.ም በአስመራ ቺቼሮ ስታዲየም እየተካሄደ ይገኛል። በውድድሩ የኢትዮጵያ ከ15 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በምድብ ሁለት ከዩጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሩዋንዳና ታንዛንያ ጋር ተደልድሎ ጨዋታውን በማድረግ ላይ ይገኛል። በምድቡ ሶስተኛ ጨዋታውን ትናንት ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሩዋንዳ አቻው  3 ለ 0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል። ቡድኑ በሶስት ጨዋታ አንድ ነጥብ ብቻ የሰበሰበውን ውጤት ተከትሎ ከምድቡ 4ኛ በመሆን ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ አልቻለም። ብሔራዊ ቡድኑ ከዚህ በፊት ባደረገቻቸው ጨዋታዎች በዩጋንዳ 3 ለ 0 ስትሸነፍ ከደቡብ ሱዳን ጋር 1 ለ 1 በሆነ የአቻ ውጤት መውጣቱ የሚታወስ ነው። ፈንቴ ፍጹም ደቡብ ሱዳን ላይ በፍጹም ቅጣት ምት ያስቆጠራት ግብ እስካሁን ለቡድኑ ብቸኛ ግብ ሆና ተመዝግባለች። ብሔራዊ ቡድኑ የመርሃ ግብር ሟሟያ የመጨረሻ ጨዋታውን እሁድ ነሐሴ 19 ቀን 2011 ዓ.ም በቺቼሮ ስታዲየም ከቀኑ 8 ሰአት ከታንዛንያ አቻው ጋር ያደርጋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምትገኝበት ምድብ ሩዋንዳና ዩጋንዳ ያደረጉትን ሁለት ጨዋታ በማሸነፍ በተመሳሳይ ስድስት ነጥብ በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል። በዚሁ ምድብ ነገ ሩዋንዳ ከታንዛንያ ዩጋንዳ ከደቡብ ሱዳን ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በምድብ አንድ ኬንያና ብሩንዳ በተመሳሳይ ሰባት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን የያዙ ሲሆን ዛሬ በምድቡ ሱዳን ከሶማሊያና አዘጋጇ ኤርትራ ከኬንያ ጋር ይጫወታሉ። ኢትዮጵያውያኑ ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴና ብሩክ የማነ ብርሃን በኤርትራ እየተካሄደ በሚገኘው የሴካፋ ከ15 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር በማጫወት ላይ ይገኛሉ። ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ በምድብ አንድ ኬንያ ከሶማሊያ፣ ሶማሊያ ከብሩንዲ እና ኤርትራ ከሱዳን ያደረጉትን ጨዋታ በመሐል ዳኝነት የመራ ሲሆን ኢንተርናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነ ብርሃን በምድብ አንድ ኬንያ ከብሩንዲ ያደረጉትን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት መርቷል። ኤርትራዊቷ ኢንተርናሽናል ዳኛ ዮዲት ሀጎስ በሴካፋ ወድድር በመሐል ዳኝነት የምታጫውት ብቸኛዋ ሴት ዳኛ ናት። የመጀመሪያው የሴካፋ ከ15 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር እስከ ነሐሴ 26 ቀን 2011 ዓ.ም ይቆያል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም