የኢኮኖሚ ባለሙያው አብደላ ሃምዶክ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ

103

ነሐሴ 16/2011 ከሦስት የሽግግር ዓመታት በኋላ ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመሻገር ጉዞዋን የጀመረችው ሱዳን አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ተሹሞላታል።

በለነፃነትና ለለውጥ ኃይሎች ተጠቁመው ወደ ስልጣን የመጡት ሃምዶክ በቀጣይ በሀገሪቱ ሰላምን ማስፈን እና ቀውስ ውስጥ የገባውን ኢኮኖሚዋን ማሻሻል ቀዳሚ ሥራቸው ነው።

በሌላ በኩል በሌተናል ጀኔራል አብደል ፋታህ ቡርሃን መሪነት ሀገሪቱን በሽግግር ጊዜ የሚያስተዳድራት ሉዓላዊ ሸንጎ በይፋ ስራውን ጀምሯል።

ጀኔራል ቡርሃን ከሦስት ዓመት በላይ የሽግግር ጊዜ ውስጥ የሉዓላዊ ሸንጎውን ለ21 ወራት በበላይነት ይመሩታል፤ የሲቪል ተወካዮች ደግሞ ቀጣዮቹን 18 ወራትን ይመራሉ።

የሽግግር መንግሥቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አብደላ ሃምዶክ የመንግሥት ቀዳሚ ሥራዎች ጦርነትን ማስቆም፣ ዘላቂ ሰላም ማስፈን፣ ኢኮኖሚያዊ ቀውስን ማርገብ እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲውን መቃኘት ናቸው ብለዋል።

አብደላ ሃምዶክ(ዶ/ር) የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚነታቸውንየለቀቁት ባለፈው  ዓመት ነበር።

ዶ/ር አብደላ ሃምዶክ በኢኮኖሚ ተንታኝነት ከ30 ዓመት በላይ ልምድ አላቸው።  ከካርቱም ዩንቨርሲቲና  ከታወቁ የእንግሊዝ ተቋሞችም ዲግሪ አግኝተዋል።

11 አባላት ያሉት የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ሸንጎ አል በሺር ከስልጣን ከወረዱበት ሚያዚያ 2019 ጀምሮ ሀገሪቱን ሲመራ የቆየውን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ተክቶ ትናንት በይፋ ስራውን መጀመሩን ቢቢሲ ዘግቧል።

ወታደራዊ ምክር ቤቱና የነጻነትና የለውጥ ኃይሎች ጥምረት የአገሪቱን የሽግግር መንግሥት ለመጀመር ባለፈው ቅዳሜ መፈራረማቸው ይታወሳል።