በዓሉ የወጣት ሴቶች ድምጽና ሀሳብ የሚሰማበት ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

198

ነሀሴ  15/2011 አሸንዳ/ ሻደይ/ አሸንድዬ/ ሶለል የወጣት ሴቶችን ድምጽና ሀሳቦች የምንሰማበት ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓሉን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕከት የአሸንዳ/ሻደይ/አሸንድዬ/ሶለል በዓል ሃይማኖታዊ መነሻ የዕርገት በዓል በመሆኑ የሰዎችን ሥነ ልቡና ከፍ በማድረግ ታላቅ ዋጋ አለው።

በዓሉ እንደ ሕዝብ የነበረንን አብሮነትና የባህል ውርርስ የሚያሳይ ክዋኔ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በዓሉ በተለያየ ስያሜ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ቢከበርም መሠረታዊ የሆነው መገለጫው ማኅበራዊና ባህላዊ ትሥሥርን የሚያሳይ ነው።

ከቀደመው ዘመን በላይ በዓሉ ዛሬ እንዲያስፈልገን የሚያደርገውም ይህ የወጣት ሴቶች ሐሳብ ነው። የማረግ ሐሳብ ፣ ከመውረድ፣ ከመዝቀጥና ተቸክሎ ከመኖር ይልቅ ወደ ላይ ተነጥቆ ማረግ፤ ይላል መልዕክታቸው።

ከቀደመው ዘመን በላይ በዓሉ ዛሬ እንዲያስፈልገን የሚያደርገውም ይህ የወጣት ሴቶች ሐሳብ ነው በማለትም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ በዓሉን በማስመልከት ያስተላለፉት መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል:-

እንኳን ለአሸንዳ/ሻደይ/አሸንድዬ/ሶለል በዓል በሰላም አደረሳችሁ! በሀገራችን ሴቶችን ወደ አደባባይ እንዲወጡ አስተዋጽዖ ሲያደርጉ ከኖሩት በዓሎቻችን መካከል አንዱ አሸንዳ/ ሻደይ/አሸንድዬ/ሶለል በዓል ነው። በዚህ ምድር አረንጓዴ በለበሰችበት በክረምቱ ወቅት በነሐሴ ወር አጋማሽ በትግራይና በአማራ ክልሎች በሚከበረው በዚህ በዓል ወጣት ሴቶች ልዩ የሆነ የሀገር ልብሳቸውን ለብሰውና ከወገባቸው ላይ እርጥብ ሰሌን በአንቀልባ መልክ አሥረው እያዜሙ ይወጣሉ።

አደባባዮቻችን በአብዛኛው በወንዶች ብቻ ተይዘው በነበረበት በዚያ ዘመን እንደ ሸንዳ/ሻደይ/አሸንድዬ/ሶለል ያሉ በዓላት መኖራቸው በበረሐ እንደተገኙ ቀዝቃዛ ምንጮች የሚቆጠሩ ናቸው። ሴቶች በግጥሞቻቸው፣ በዜማዎቻቸውና በጭፈራዎቻቸው ሐሳባቸውን፣ ባህላቸውንና ምኞታቸውን እንዲገልጡ በማድረግም የማይተካ ሚና ነበራቸው። ለዚህም ነው እስከዛሬም ድረስ ወጣት ሴቶች ዓመቱን በሙሉ በጉጉት የሚጠብቁት በዓል የሆነው።

የነሐሴ ወር፣ አንድ በዓል ለወንዶች አንድ በዓል ለሴቶች በመስጠት ፍትሐዊነቱን ያሳየ ወር ነው። ወጣት ወንዶች ችቦ ለኩሰው፣ ዳስ ሠርተው፣ ጅራፍ እያስጮኹ የቡሄን በዓል ያከብሩታል። ጭፈራው፣ ሆታው የወጣት ወንዶችን ሐሳብ የምንሰማበት፣ የደረሱበትን ደረጃ የምንለካበት፣ የነገውንም ምኞታቸውን የምናውቅበት ነው። እንዲሁም አሸንዳ/ ሻደይ/ አሸንድዬ/ ሶለል ደግሞ የወጣት ሴቶችን ድምጽና ሀሳቦቻቸዉን የምንሰማበት ወቅት ነው።

የአሸንዳ/ሻደይ/አሸንድዬ/ሶለል በዓል እንደ ሕዝብ የነበረንን አብሮነትና የባህል ውርርስ የሚያሳይ ክዋኔ ነው። በዓሉ በተለያየ ስያሜ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ቢከበርም መሠረታዊ የሆነው መገለጫው ማኅበራዊና ባህላዊ ትሥሥርን የሚያሳይ ነው።

የአሸንዳ/ሻደይ/አሸንድዬ/ሶለል በዓል ሃይማኖታዊ መነሻ የዕርገት በዓል በመሆኑ የሰዎችን ሥነ ልቡና ከፍ በማድረግ ታላቅ ዋጋ አለው። ከቀደመው ዘመን በላይ በዓሉ ዛሬ እንዲያስፈልገን የሚያደርገውም ይህ የወጣት ሴቶች ሐሳብ ነው። የማረግ ሐሳብ። ከመውረድ፣ ከመዝቀጥና ተቸክሎ ከመኖር ይልቅ ወደ ላይ ተነጥቆ ማረግ።

ታዋቂው የሀገራችን ደራሲ ሰሎሞን ዴሬሳ

“ዳገት፣ ሽቅብ የታየ ቁልቁለት

ቁልቁለት፣ ቁልቁል የታየ ዳገት”

በማለት እንደገለጠው ዳገትና ቁልቁለት የአተያይ ጉዳዮች ናቸው። የት ጋ ነው የቆምነው? የሚለው ነው ወሳኙ። ችግርን ከሥሩ ሆነን ከተመለከትነው ያስፈራራናል፤ ሊጫነንም ይደርሳል፤ ያንን የችግር ቁልል መናድ የማይሞከር መስሎ ይሰማናል። ችግርን እንደ ንሥር ከላዩ ሆነን ስናየው ግን ቀልሎና ኢምንት ሆኖ ይታየናል። ልንንደው፣ ልናስወግደው እንደምንችል እናምናለን። ከከፍታ ወርደን ታች ለመድረስ ቁልቁለቱ ይቀለናል፣ ያንን የወረድነውን መልሰን መውጣት ግን ዳገት ይሆንብናል። ሆኖም የት እንደነበርን ማስታወስ ከዳገቱ የበለጠ አቅም እንዳለን እንድንረዳ ያደርጋል። የወረድነውን ዳገት መልሰን መውጣት ብቻም ሳይሆን ከዚያም በላይ ከፍ ማለት እንደምንችል እንድንረዳ ያደርገናል።

ለዚህ ነው ችግርን ለማስተካከል ከመነሣታችን በፊት አስቀድመን ችግሩን የምናይበትን ቦታ ማስተካከል የሚያስፈልገን። ማረግ የሚያስፈልገንም ለዚህ ነው። ችግሮቻችንን ከበላያቸው ሆነን ለማየት እንድንችል። ኢትዮጵያን ተብትበው የያዟት አያሌ ችግሮች ሊፈቱና እስከመጨረሻው ሊወገዱ እንደሚችሉ የሚያምኑም የማያምኑም አሉ። የሁለቱ ልዩነት ካገኙት መረጃና ካካበቱት ዕውቀት የሚመጣ አይደለም። ከቆሙበት ቦታ የሚመነጭ ነው። እንደ አሸንዳ/ሻደይ/አሸንድዬ/ ሶለል ወጣት ሴቶች ለማረግ የወሰኑ፣ ችግሮቹን ከላያቸው ሆነው ያዩዋቸዋል። ራሳቸውንም ከችግሮቹ በላይ ያገኙታል። እንደ እነዚህ ወጣት ሴቶች ለዕርገት ያልተዘጋጁት ግን ራሳቸውን ከችግሮቹ ሥር ወድቆ ያገኙታል። ያኔ ተስፋ ይቆርጣሉ።

 

ኑ፤ እንደ አሸንዳ/ ሻደይ/አሸንድዬ/ ሶለል ወጣት ሴቶች እናርግ። ይህ በዓል ሺ ዘመናትን ያስቆጠረ በዓል ነው። በደስታ ዘመናት ብቻ ሳይሆን በአስቸጋሪዎቹ ዘመናትም ሲከበር ኖሯል። ለእኅቶቻችን ጉዳዮች ትኩረት ባልሰጠንበትና ሴቶች ከማጀት እንዳይወጡ አሥሮ በሚይዘው ዘመን ይህ በዓል ይከበር ነበር። እኅቶቻችን ዙሪያቸውን በአያሌ የመብት ጥሰቶች ተከብበው፣ በዕንቅፋትና በጫና ተይዘው እንኳን፣ ተስፋ መቁረጥ የሚባል አልነካቸውም። ተስፋ ቢቆርጡ ኖሮ ወደታች እንዲወርዱ በሚያደርገው ዘመን ወደ ላይ የማረግን በዓል ባላከበሩት ነበር።

ለችግሮቻቸው ከመንበርከክ ይልቅ ችግሮቻቸውን መናቅ ፈለጉ። ለዚህም ነው ከላይ ሆነው ማየትን የመረጡት። ሕዝባችን አስቸጋሪ ፈተናዎችን ተጋፍጦ እንዲያልፍ የሞራል ስንቅ ከሆኑት ነገሮች መካከል እንዲህ ያሉት የልዕልና አስተሳሰቦች ዋጋቸው የማይተመን ነው። ከእነዚህ ወጣት ሴቶች የማረግን ሐሳብ፣ የከፍታንም ምኞት እንቅሰም። ችግሮቻችንንም ከበላያቸው ሆነን እንናዳቸው፤ ያን ጊዜ በቀላሉ እንፈረካክሳቸዋለን። ኑ፣ አብረን ከአሸንዳ/ ሻደይ/ አሸንድዬ/ሶለል ወጣት ሴቶች ጋር እናርግ።

መልካም የአሸንዳ/ሻደይ/አሸንድዬ/ሶለል በዓል።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ነሐሴ 15 ቀን 2011 ዓ.ም