የእግረኛ መንገዶች ለተጨማሪ አካል ጉዳተኝነት እያጋለጡን ነው – አይነስውራን

1580

ሰኔ 7/2010 የእግረኛ መንገዶች ምቹ አለመሆንና በመንገዶቹ ላይ የሚከናወኑ ተግባራት እንቅስቃሴዎቻቸውን አስቸጋሪ እንዳደረጉባቸው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አይነስውራን ገለጹ፡፡

በተመሳሳይ በመዲናዋ የትራፊክ መብራቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ለአይነስውራን የድምጽ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች አለመኖርም በዕለት ከእለት እንቅስቃሴያቸው ላይ ተጽዕኖ እያሳደረባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወጣቷ አይነስውር ካሰች ድሉ እንደምትለው እርሷና መሰሎቿ ጠዋት የተጓዙበት መንገድ ሲመለሱ ተቆፋፍሮ ስለሚጠብቃቸው ለተጨማሪ ጉዳት እየተጋለጡ ናቸው፡፡

ለዚህም ጠዋት ለስራ አብሯት የወጣ አይነስውር ጓደኛዋ በእግረኛ መንገድ ላይ በተቆፈረ ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ ጉዳት እንደደረሰበት ለአብነት አንስታለች፡፡

ልማቱን ለማስፋፋት የሚደረገው ጥረት ተገቢ ቢሆንም ልማቱ አንዱን ጠቅሞ ሌላውን የሚጎዳ ሳይሆን አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ እንዲሆንም ጠይቃለች፡፡

በደጃዝማች በላይ ዘለቀ ቁጥር አንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአስረኛ ክፍል ተማሪው ፋንታሁን አበራ እንደሚለው ደግሞ  ከምሰሶዎችና ያለስራ ክፍት ከተተው ጉድጓዶች በተጨማሪ በእግረኛ መንገዶች ላይ የሚከማቹ የግንባታ እቃዎችና የወደቁ ዛፎች ያደነቃቅፏቸዋል፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ አብርሃም ደቦጭም  “ቢጫው  ቀለም ለሚያዩት እንጂ ለኛ ምንም የሚሰጠው ፋይዳ የለም፤ ሲረገጥ እንኳ በእግር መለየት የማይቻል ምልክትነው፤ መንገዱን ተከትለን ስንሄድም ከኤሌክትሪክ ምሰሶ ጋር ነው የምንጋጨው፤ ጉድጓድ ውስጥ ነው የምንገባው” ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት በምሬት ተናግረዋል፡፡

አቶ መሀመድ ኑር የድምጽ መልዕክት ማስተላለፊያ መሳሪያዎች በየአደባባዮች ባለመገጠማቸው ለጥገኝነት ከመዳረጋቸውም በላይ አንዳንድ ሰዎች “እናሻግራችሁ” በሚል  አቅጣጫ አስተው ጥቃት እንደሚያደርሱባቸው ገልጸዋል፡፡

ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ተማሪ ለምለም ድንቁም የድምጽ መልዕክት ማስተላለፊያ መሳሪያዎች በሌሉባቸው አደባባዮች የትራፊክ ፍሰቱን ከአራቱም አቅጣጫ በድምጽ ለይታ ለመንቀሳቀስ እንደተቸገረች ተናግራለች፡፡

በኢትዮጵያ አይነስውራን ማህበር የህዝብ ግኑኝነት፣ የቅርንጫፎችና የአባልነት ጉዳይ ኃላፊው አቶ ገብረ ህይወት ተሾመ እንዳሉት አይነስውራንን ታሳቢ ያደረጉ መንገዶች እንደ ጅምር መልካም ቢሆኑም ክፍት ጉድጓዶች፣ የመብራትና የስልክ ምሰሶዎችና ሌሎች አደናቃፊ ነገሮች አይነስውራንን ለተጨማሪ ጉዳት እየዳረጓቸው ይገኛሉ፡፡

ካለፈው ዓመት ጀምሮ የችግሩን አሳሳቢነት ለአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በደብዳቤ ቢያሳውቁም እስካሁን መፍትሔ አለመገኘቱንም ነው ያብራሩት፡፡

በአዲስአበባ መንገዶች ባለስልጣን የኮምዩኒኬሽን ዳይረክተሩ አቶ ጥኡማይ ወልደገብርኤል ለአይነስውራን በተዘጋጀው ልዩ መስመር ላይ የሚካሄዱ ቁፋሮዎችን ጨምሮ አትክልቶችን፣ ምሰሶዎችንና መሰል እንቅፋቶችን በተመለከተ ኢዜአ ላነሳላቸው ጥያቄዎች “በቀጣይ ትኩረት ይደረግባቸዋል” ከሚል ያለፈ አጥጋቢ ምላሽ አልሰጡም፡፡

ከትራፊክ ድምጽ አገልግሎቱ ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ታመነ በሌ በሰጡት ምላሽ አገልግሎቱ በ19 አካባቢዎች ተጀምሮ እንደነበር አስታውሰው ማሻሻያ በማስፈለጉ አገልግሎቱ መቋረጡን ተናግረዋል፡፡

የማሻሻያ ስራው በመጠናቀቁ  በበጀት ዓመቱ መጨረሻ በነባሮቹና በአዳዲስ አካባቢዎች የትራፊክ ድምጽ መልዕክት አገልግሎቱ እንደሚጀመር አረጋግጠዋል፡፡