አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ-ካርታ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚተገበር የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ

224
ነሀሴ 15 ቀን 2011 (ኢዜአ) አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ-ካርታ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ስራ እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ አዲሱን የትምህርትና ስልጠና  ፍኖተ-ካርታ አተገባበርና ይዘት በተመለከተ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል። ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ፍኖተ ካርታውን ሙሉ ለሙሉ ወደ ተግባር ለመቀየር የ5 ዓመት ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል ። ከሚተገበሩት ለውጦች መካከልም ዘንድሮ ወደ 9ኛ ክፍል የሚገቡ ተማሪዎች በአስረኛ ክፍል የሚያጠናቅቁ ሳይሆን የአራት ዓመት የትምሀርት ቆይታ የሚያደርጉበት ነው ብለዋል። ከአዲሱ ዓመት ጀምሮ የሶስት ዓመት የዩኒቨርሲቲ ቆይታ እንደማይኖር የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የሶስት ዓመት ቆይታ ወደ አራት ዓመት ከፍ ማለቱንና  በመጀመሪያው ዓመት ሁሉም ተማሪዎች የአገራቸውን ታሪክና ጂኦግራፊን ጨምረው የተግባቦት ትምህርቶችን የሚያውቁበት ነውም ብለዋል። የኢንጂነሪንግ፣ የህግ፣ የፋርማሲና ሌሎች  የ4-5-6 ዓመት ፕሮግራም ያላቸው የትምህርት መስኮች ደግሞ  በነበሩበት እንደሚቀጥሉ ተገልጿል። አዲሱ የትምህርት መዋቅር በሶስት ክፍሎች ተመድቦ የሚሰራበት ሲሆን እሱም (የ6-2-4) ቅርጽ የሚኖረውና ይህም የ6 ዓመት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት፤ የ2ዓመት የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምሀርትና የ4 ዓመት ደግሞ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት እንዲሆን መወሰኑንም አስታውቋል። በዚህም ተማሪዎች የ8ኛ ክፍል ሲያጠናቅቁ ብሄራዊ  ፈተና የሚወስዱ ሲሆን የ6ተኛ ክፍልን ሲያጠናቅቁ ደግሞ ክልላዊ ፈተና የሚወስዱ ይሆናል ነው የተባለው። በፍኖተ ካርታው ከተካተቱት መካከል በመልካም ስነ-ምግባር  የበለጸጉ ዜጎችን ከማፍራት አኳያ የትምህርት ስርዓቱ ላይ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ የስነ-ምግባርና የስነ-ዜጋ ትምህርቱ በግብረገብ ትምህርት ተተክቶ በትኩረት የሚሰጥ ሲሆን ከዚያ በኋላም በየደረጃው የስነ ዜጋ ትምህርት ይሰጣልም ተብሏል። ይህም በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ ተማሪዎች አገራዊ አንድነቱን የሚያጠናክርና የሚያስቀጥል ስነ ምግባር ተላብሰው ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል። የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋምን በተመለከተም ሁሉም መደበኛ የሙያ ስልጠና መስኮች ከ12ኛ ክፍል በኋላ የሚሰጡ መሆኑን በመግለጫው ተጠቁሟል። የመምህራን ምደባን በተመለከተም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪ ባላቸው መምህራን፣ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል  የሁለተኛ ዲግሪ ባላቸው መምህራንና ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ደግሞ የሁለተኛና ከዚያ በላይ ዲግሪ ባላቸው እንደሆነ ሚኒስቴሩ አስታውቋል። የቴክኒክና ሙያ ደረጃ አንድና ደረጃ ሁለት የሙያ ስልጠና የመጀመሪያ ደረጃ ዲግሪ ባላቸው የደረጃ አራትና አምስት ደግሞ የማስተረስ ዲግሪና ከዚያ በላይ ባላቸው አሰልጣኞች እንዲሰጥ የሚደረግ እንደሚሆንም አስታውቋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም