ኢጋድ በደቡብ ሱዳን በሶስት ወራት ውስጥ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት አሳሰበ

84
ነሐሴ 15/2011  የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ተጠናቆ የሽግግር መንግስቱ መመስረት እንደሚገባው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) አሳሰበ። የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ካለፈው ግንቦት ወር በኋላ የተከናወነው አፈጻጸም በአዲስ አበባ ተገምግሟል። ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ በአገሪቷ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑም በዚሁ ጊዜ ተነግሯል። የኢጋድ የወቅቱ ሊቀመንበርና የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ  ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው እንዳሉት በደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች ባለፈው ግንቦት ወር በደረሱት ስምምነት መሰረት በአገሪቱ የተኩስ አቁም ተግባራዊ ሆኗል። በዚህም የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት በዋና ከተማዋ ጁባ በተሻለ ነፃነት እየተንቀሳቀሱ መስራት ችለዋል። የተኩስ አቁም ገቢራዊ መሆኑ የተደረሰው ስምምነት ውጤታማ መሆኑን ያሳያል ያሉት ሊቀመንበሩ ይሁን እንጂ  በተቀናቃኞች መካከል አሁንም አለመተማመንና በሰላም ጉዳይ አብሮ የመስራት ፍላጎቱ ደካማ ነው ብለዋል። በዋና ዋና ጉዳዮች ላይም ባለፉት ወራት የታየው አፈጻጸም ዝቅተኛ እና  በሚፈለገው መጠን አለመከናወኑን አስረድተዋል። የሰላም ፈራሚ አካላቱ ያሏቸውን ሰራዊቶች ወደ ካምፕ ለመመለስና አንደ ሰራዊት ለማቋቋም ስምምነት ላይ ደርሰው የነበረ ቢሆንም እስካሁን ተግባራዊ አላደረጉም። አገሪቷ ምን ያህል ክልሎች ሊኖሯት እንደሚገባና የክልሎቹ ወሰን ላይም የጋራ መግባባት ላይ አለመድረሳቸው ተነግሯል። በቀጣዮቹ ወራቶች እነዚህ ጉዳዮች ላይ  በመስማማት ለሽግግር መንግስቱ ምስረታ ምቹ ሁኔታን ማመቻቸት እንዳለባቸው የሰላም ሰምምነቱ አደራዳሪ አካላት ጥሪ አቅርበዋል። በደቡብ ሱዳን የሽግግር መንግስት ለመመስረት ሲደረግ የነበረው ድርድር ለሁለት ጊዜያት መራዘሙ ይታወሳል። ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያት የአገሪቷ የሰላምና ደህንነት ጉዳይ በሚፈለገው መጠን ውጤታማ ባለመሆኑ ነው። የሰላም ስምምነቱ ተፈፃሚ ሆኖ ከመጭው ጥቅምት ወር አጋማሽ  ቀደም ብሎ የሽግግር መንግስት መመስረት እንዳለበት ኢጋድ አሳስቧል። ይህ ካልሆነ ግን ሀገሪቱ የከፋ ቀውስና አለመረጋጋት  ውስጥ ልትገባ ትችላለች ሲል አስጠንቅቋል። በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ሁለቱ ተደራዳሪ አካላት ለአገሪቷ  ሰላም ቅድሚያ ሰጥተው እንዲሰሩ ጥሪውን አቅርቧል። ከአምስት ዓመታት በላይ በዘለቀው የደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት አስር ሺዎች የአገሪቷ ዜጎች ሕይወታቸውን ሲያጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም