በጋምቤላ የአርሶና ከፊል አርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በቅንጅት መስራት ይገባል....አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

69
ጋምቤላ (ኢዜአ) ነሀሴ 15 ቀን 2011- በጋምቤላ ክልል የግብርና ቴክኖሎጂዎችንና መልካም ተሞክሮችን በማስፋት የአርሶና ከፊል አርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት አንዲሰሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስገነዘቡ።ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በሁለት የክልሉ ወረዳዎች በግብርናው ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በእዚህ ውቅት እንደገለጹት የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችንና ምርጥ ተሞክሮዎችን በማስፋት የአርሶና ከፊል አርብቶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተግተው ሊሰሩ ይገባል። በክልሉ ቀደም ሲል የነበሩ ኋላቀር የግብርና አሰራሮችን ወደ ዘመናዊ አሰራር በማሸጋገር ምርታማ አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮችን በብዛት ለመፍጠር አመራሮችና የግብርና ባለሙያዎች ጠንክረው እንዲሰሩም አስገንዝበዋል። በዘንድሮ ዓመት በተወሰኑ አርሶ አደሮች የተጀመረው ሰብል በኩታ ገጠም የማልማት ስራ ውጤታማ መሆኑን በመስክ ምልከታቸው እንዳረጋገጡም አቶ ኡሞድ ተናግረዋል ። የተጀመረው የኩታ ገጠም የሰብል ልማት ሥራ ወደ ሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ሊሰፉ እንደሚገባ ጠቁመው፣ “ለዘርፉ መጠናከር የክልሉ መንግስት ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሎው ኡቡፕ በበኩላቸው የዘንድሮው የመኸር እርሻ ሥራ በተሻለ ዝግጅትና ንቅናቄ መጀመሩን ተናግረዋል። በምርት ዘመኑ ከ124 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የሰብል አይነቶችና የጓሮ አትክልቶች ለማልማት ታቅዶ እስከ ሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም ድረስ ከ78 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ማልማት መቻሉን ገልጸዋል። ያለማውን ቀሪ መሬት ዘግይተው በሚዘሩ የሰብልና የአትክልት ዓይነቶች ለማልማት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ሎው፣ በምርት ዘመኑ ከ3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን አመልክተዋል። በኢታንግ ልዩ ወረዳ በኤሌያ ቀበሌ በግብርና ልማት ተሰማረተው ያገኘናቸው እማውራ ወይዘሮ አባላ ኦቦንግ በሰጡት አስተያየት ከልማት ጣቢያ ባለሙያዎች በአገኙት ስልጠና ታግዘው ለውዝና ሌሎች የሰብል ዓይነቶችን እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል። በግብርና ባለሙያዎች በተፈጠረ አደረጃጀት እንዲሁም የእርሻ መሳሪያ ድጋፍና ጥሩ የዝናብ ስርጭት መኖሩ ሰብላቸው በተሻለ አንዲለማ ማድረጉን የገለጹት ደግሞ የአበቦ ወረዳ የሸቦ መንድር 13 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ዳሻ ፍቃዱ ናቸው። ሌላው የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አደነ ሌሎ በሰጡት አስተያየት በዘንድሮው ዓመት በመሬታቸው ወሰንተኛ ከሆኑ አርሶ አደሮች ጋር ተመሳሳይ ሰብል በጋራ ማልማት መጀመራቸውን ተናግረዋል። “የኩታ ገጠም የሰብል ልማት እርስ በእርስ ለመደጋገፍም ሆነ በሰብል ላይ ጉዳት የሚያደረሱ ተባዮችን በጋራ ለመከላከል አዋጭ ዘዴ በመሆኑ በቀጣይ አጠናክረን እንቀጥልበታለን” ብለዋል። በጋምቤላ ክልል ባለፈው ዓመት የመኸር እርሻ ልማት ከ72 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ለምቶ እንደነበር ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም