የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመልስ ጨዋታውን ለማድረግ ወደ ታንዛኒያ አቀና

116

አዲስ አበባ ኢዜአ ነሀሴ 15/2011 የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመልስ ጨዋታውን ለማድረግ ወደ ዛሬ ታንዛኒያ አምርቷል።
የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ የመልስ ጨዋታዎች የፊታችን ቅዳሜና እሁድ ይካሄዳሉ።

ኢትዮጵያን በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የወከለው የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ ቅዳሜ ነሐሴ 18 ቀን 2011 ዓ.ም በዳሬሰላም ከተማ አዛም ኮምፕሌክስ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰአት ላይ ከአዛም አቻው ጋር የመልስ ጨዋታውን ያደርጋል።

ፋሲል ከነማ ከታንዛኒያው ክለብ ጋር ላለበት የመልስ ጨዋታ ዛሬ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ወደ ዳሬሰላም አቅንቷል።

ነሐሴ 5 ቀን 2011 ዓ.ም በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በተደረገው የመጀመሪያው ጨዋታ ፋሲል ከነማ በዛብህ መለዮ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ተጋጣሚውን 1 ለ 0 በሆነ ውጤት ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

የፋሲል ከነማ አሰልጣኝ የነበረው ውበቱ አባተ በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከተደረገው ጨዋታ በኋላ ከክለቡ ጋር የተለያየ ሲሆን ፋሲል ከነማ በውበቱ ምትክ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ የሁለት ዓመት ውል በማስፈረም የክለቡ አሰልጣኝ አድርጎ መሾሙም ይታወቃል።

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ክለቡን ከተረከቡ በኋላ በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየምና ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ለመልሱ ጨዋታ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል።

ክለቡ የመጨረሻ ልምምዱን ትናንት ከረፋዱ አራት ሰአት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም አድርጓል።

በአህጉራዊ የክለብ ውድድር የመጀመሪያ ተሳትፎው የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረው በዛብህ መለዩ በደረሰበት ጉዳት ከመልሱ ጨዋታ ውጪ ሆኗል።

በብሩንዲያዊው አሰልጣኝ ኢቲዬን ንዳዪራጊጄ የሚሰለጥነው የታንዛኒያው ክለብ አዛም ከፋሲል ከነማው ሽንፈት በኋላ ነሐሴ 11 ቀን 2011 ዓ.ም በታንዛንያ ኮምዩኒቲ ሺልድ ባደረገው ጨዋታ በተቀናቃኙ ሲምባ 4 ለ 2 መሸነፉ የሚታወስ ነው።

አዛም ውጤቱን ቀልብሶ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ከሁለትና ከዚያ በላይ የጎል ልዩነት በሆነ ውጤት ማሸነፍ ይጠበቅበታል።

በአንጻሩ ፋሲል ከነማ ማሸነፍ 0 ለ 0 እና 1 ለ 1 መውጣት 2 ለ 1 መሸነፍ በአጠቃላይ ክለቡ ግብ አስቆጥሮ በአንድ ጎል ልዩነት መሸነፍም ወደ ቀጣዩ ዙር ያሳልፈዋል።

ፋሲል ከነማ በደርሶ መልስ ውጤት ተጋጣሚውን ካሸነፈ በመስከረም ወር 2012 ዓ.ም ከዚምባቡዌው ትሪያንግል ዩናይትድና ከብሩንዲው ሩኪንዞ አሸናፊ ጋር ይጫወታል።

በመስከረም ወር 2012 ዓ.ም የሚያደርገውን ጨዋታ በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈ ወደ ምድብ ድልድል ውስጥ ይገባል ማለት ነው።

የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ ዛሬ ወደ ስፍራው ያቀና ሲሆን የክለቡ ደጋፊዎችም ክለባቸውን ለመደገፍ አርብ ነሐሴ 17 ቀ 2011 ዓ.ም ወደ ዳሬሰላም እንደሚያቀኑ ከክለቡ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በሌላ በኩል በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈው መቐለ ሰብዓ እንደርታ የማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን እሁድ ነሐሴ 19 ቀን 2011 ዓ.ም በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከኢኳቶሪያል ጊኒው ክለብ ካኖ ስፖርት አካዳሚ ጋር ያደርጋል።

ነሐሴ 4 ቀን  ዓ.ም በተደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ካኖ ስፖርት አካዳሚ በጆሴ ፔድሮ ኦቢያንግና ጆሴ ፊደል ሲፒ ጎሎች መቐለ ሰብዓ እንደርታን 2 ለ 1 በሆነ ውጤት ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

ለመቐለ ሰብዓ እንደርታ በአህጉራዊ የክለብ ውድድር ተሳትፎ የመጀመሪያ ግቡን አማኑኤል ገብረሚካኤል ማስቆጠሩም የሚታወቅ ነው።