በዓሉ በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን የደህንነት ዝግጅት አድርገናል-የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን

1401

 አዲስ አበባ ሰኔ 7/2010 የረመዳን ፆም ፍቺ በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን የደህንነት ዝግጅት ማድረጉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፈንታ ለኢዜአ እንዳስታወቁት በዓሉን በማስመልከት  “ከእምነቱ ተከታዮችና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት ዝግጅቱን አጠናቀናል” ብለዋል።

በዓሉ አርብ ወይም ቅዳሜ ይከበራል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በተለይም በፖሊስ ሊደረጉ የሚገቡ የቁጥጥር፣የፍተሻና ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር  በቅንጅት ለመስራት በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ለማክበር ወደ እምነት ተቋማት በሚሄድበት ወቅትም የመኖሪያ ቤቱን ደህንነት ለመጠበቅ እንዲሁም ምዕመናኑ ተሰባስበው በሚያከብሩባቸው አካባቢዎች የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይኖር የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶችም  ተደርገዋል ብለዋል።

በዚህም መሰረት በአዲስ አበባ ስታዲየም አካባቢ ያሉ መተላለፊያ መንገዶች ማለትም ከአራት ኪሎ በቤተ መንግስት ወደ ስታዲዮም የሚወስደው፣ ከሰንጋ ተራ በጥቁር አንበሳ ወደ ብሄራዊና ስታዲየም የሚወስደው፣ ከለገሃር ወደ ሜክሲኮ የሚወስደውና  ሌሎች መስቀል አደባባይን የሚያቋርጡ መንገዶች  በበዓሉ እለት ለትራፊክ ዝግ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

አሽከርርካሪዎች ይህን በመገንዘብ አማራጭ መንገዶችን በመጠቀም እንዲተባበሩም ጠይቀዋል።

በዓሉን በሰላም ለማክበርም ህዝበ ሙስሊሙና ሌላው ማህበረሰብ ማንኛቸውንም ወንጀል ነክና ለደህንነት አጠራጣሪ የሆኑ ነገሮችን ለአካባቢው ፖሊስ  በመጠቆም የተለመደ ትብብራቸውን እንዲያደርጉም  ጥሪ አቅርበዋል ኮማንደር ፋሲካ።