”ወጣቶች ሥራ ሳይንቁ በትጋት ከሰሩ ስኬታማ የይሆናሉ ” -ወጣቷ ሥራ ፈጣሪ

80

ማይጨው ነሐሴ 14 ቀን 2011 ”ወጣቶች ሥራ ሳይንቁና ሳያማርጡ በተሰማሩበት ሥራ በትጋት ከሰሩ ስኬታማ መሆን እንደሚችሉ ከእኔ መማር ይችላሉ” የምትለው የኮረም ሥራ ፈጣሪዋ ወጣት።

ወይንሸት አማረ በመንገድ የድንጋይ ንጣፍ(ኮብል ስቶን)ሥራ ተሰማርታ ባገኘችው  መነሻ ገንዘብ የሯሷ ፈጠራ ወደ ሆነው የሻማ አምራችነት የተሸጋገረችው ወጣት ናት።

በትግራይ ክልል በኮረም ከተማ ተወልዳ ያደገችው ወይንሸት ከቤተሰብ ጥገኝነት ተላቃ ለሌሎች ወጣቶችም ሥራ ፈጥራለች።

በከተማው የቴክኒክና ሙያ ትምህርቷን አጠናቅቃ የመንግሥትን ሥራ ሳትጠብቅና ሥራ ሳትንቅ በድንጋይ ንጣፍ ሥራ ላይ መሰማራቷን ትናገራለች።

ከዚህም ተነስታ በሦስት ዓመታት ውስጥ ወደ ሻማ ማምረትና ማከፋፈል ሥራ መግባቷን ትገልጻለች።

በአዲስ አበባ ለሦስት ወራት በወሰደችው ስልጠና ሥራ ለመጀመርም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድር በመውሰድ ዘመናዊ የሻማ ማምረቻ ማሽን ገዝታ ሥራ ጀመርኩ ትላለች።

በሥራዋ  ያጠራቀመችውን 60 ሺህ ብርና በብድር ከወሰደችው 100 ሺህ ብር  ጋር በማዳመር አዲሱ ሥራዋን ቀጠለች።

በቀን እስከ 500 ሻማዎች የምታመርተው ወጣት ወይንሸት፣አሁን ብድሯን ሙሉ በሙሉ ከፍላ ማጠናቀቋን ትናግራለች።

መደበኛና የጌጥ ሻማዎችን በማምረትና በማከፋፈል የተሰማራችው ወጣት ወይንሸት፣ምርቷን በትግራይ ክልል በማዳረስ ወደ ሌሎች ክልሎችም የማስፋፋት ዕቅድ አለኝ ብላለች።

ከዚህም ባለፈ ከሻማ ምርት ባገኘችው ትርፍ የአልባሳት መሸጫ ሱቅ ከፍታለች።

እንደ ወይንሸት ገለጻ ከሆነ፣ሥራው ውጤታማ እንደሚሆን በማመንና ገበያን በማጥናት ስለገባሁበት ስኬታማ ሆኛለሁ ትላለች።

ሌሎች ሥራ አጥ ወጣቶችም ሥራ ሳይንቁና ሳያማርጡ በአገራቸው ውስጥ ተግተው ከሰሩ ስኬታማ የማይሆንበት ሁኔታ የለም በማለት ምክሯን ለግሳለች።

መንግሥት ባመቻቸው የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ የሆነውና የኮረም ከተማ ነዋሪ ወጣት እስጢፋኖስ መብራህቱ ወጣቷን ሥራ ፈጣሪ ከተማሪነት ጀምሮ እያለችም እንደሚያውቃት ይናገራል። ”እጅግ ታታሪ” ይላታል።

ወይንሸት ሥራ ሳትንቅ ጠንክራ በመሥራቷ የስኬቷ ምስጢር ነው ብሏል።ጥረቷ ለሌሎች ወጣቶችም አርአያ መሆኑንም ይገልጻል።

የኮረም ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሐፍቶም ዋዬ እንዳሉትም፣በከተማው ከስድስት ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሥራ አጥ ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን አስታውቀዋል።

ሥራ አጥ ወጣቶች ሥራ እንዲፈጥሩና ስኬታማ እንዲሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የከተማው ወጣቶች ከወይንሸትና መሰል ስኬታማ ወጣቶች በመማር ለውጤት እንዲበቁም መሥራት እንደሚገባቸው ያሳሰቡት አቶ ሸፍቶም፣ወጣቶቹ በተሰማሩበት የስራ መስክ ስኬታማ እንዲሆኑ ድጋፍ ይደረግላቸዋል ብለዋል።