በታሪክ ቅብብሎሽ ውስጥ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ሚናቸውን ማጎልበት እንዳለባቸው ተጠቆመ

89

መቀሌ ኢዜአ ነሐሴ 14/2011፡- በታሪክ ቅብብሎሽ ውስጥ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ያላቸውን ሚና ለማጓልበት ተግተው መስራት እንዳለባቸው ተጠቆመ።

የትግራይ የኪነጥበባት ባለሙያዎች ማህበር አምስተኛ መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ በመቀሌ ከተማ ተካሂዷል።

በጉባኤው የተገኙት የክልሉ የመንግስትና ህዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊያ ካሳ እንዳሉት፣ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ የህዝብ አንድነት እንዲጠናክር የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የጎላ ሚና ነበራቸው።

የትግራይ ህዝብ ይደርስበት ከነበረው ጭቆና ለመላቀቅ ባካሄደው ተጋድሎ ውስጥ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ አስታውሰው ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግን መንግስት አስፈላጊውን ትኩረት ሳይሰጠው መቆየቱን ተናግረዋል።

በታሪክ ቅብብሎሽ ውስጥ የባለሙያዎቹ ሚና ቀላል አለመሆኑን ጠቅሰው ሙያቸውን በመጠቀም ህዝቡ ሚዛናዊ አስተሳሰብ እንዲይዝ ይበልጥ መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

በትግራይ በየዓመቱ የሚካሄደው የባህል ፌስቲቫል የክልሉን ባህልና ታሪክ በሚያንፀባርቅ መልኩ እንዲከናወን የኪነጥበብ ባለሙያዎቹ ሚና የጎላ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ብርኽቲ ገብረመድህን ናቸው።

የማህበሩ ቦርድ ሰብሳቢ አርቲስት ምስጉን ተስፋዬ እንደገለጹት የማህበሩ አባላት አቅማቸውን ለማጎልበት በተለያዩ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት እድል እንዲያገኙ እየተደረገ ነው።

የታሪክ ቅብብሎሹ እንዲጠናከርና የክልሉን ህዝብ ደማቅ ታሪክ  ለትውልድ እንዲተላለፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በጉባኤው አስተያየታቸውን የሰጡ የኪነጥበብ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።

የማህበሩ አባላት ባለፉት ሶስት ዓመታት የተከናወኑትን ስራዎች በጉባኤው የገመገሙ ሲሆን፣ በቀጣይ የሚሰሩ የቦርድ አመራሮችም ተመርጠዋል።