ህፃናት አገር ተረካቢ ዜጋ ሆነው ያድጉ ዘንድ ሳይንሳዊ የሆነ አስተዳደግን ሊያገኙ ይገባል

91

አዲስ አበባ ኢዜአ ነሀሴ 14/2011 ህፃናት በራሳቸው የሚተማመኑ፣ በአካልና በአእምሮ የበቁ አገር ተረካቢ ዜጋ ሆነው ያድጉ ዘንድ ሳይንሳዊ የሆነ አስተዳደግን ሊያገኙ ይገባል ተባለ። በህፃናት አያያዝ ‘ሞግዚትነት’ ሙያ የሰለጠኑ 450 ሥራ አጥ ሴቶች ዛሬ ተመርቀዋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጋቱ ዳኛቸው ለኢዜአ እንደገለፁት ሁለንተናዊ ጤንነቱ የተጠበቀ ብቁ ትውልድን ለመፍጠር መሰረት ለሆኑት ህጻናት ተገቢውን አስተዳደግ ማመቻቸት እንደሚጠይቅ ገልፀዋል።

ለዚህ ደግሞ በሙያው ሳይንሳዊ እውቀትን የተላበሱ ብቁ ሙያተኞች እንደሚያስፈልጉ አቶ ንጋቱ ተናግረዋል።

መንግስት ይህንን ጨምሮ የቴክኒክና ሙያ ስልጠናን በየደረጃው በማሳደግ ብቃት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልፀዋል።

ሴቶች በተለያዩ የሙያ መስኮች ሰልጥነው ወደስራ እንዲገቡ ከተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።

ለሴቶች እየተመቻቹ ካሉት የስልጠና ዘርፎች መካከል የህጻናት አያያዝና እንክብካቤ ሙያ ይገኝበታል ብለዋል።

ይህም መንግስት በሁሉም መስሪያ ቤቶች ቢሮዎች ውስጥ የህፃናት ማቆያ ለመክፈት የያዘውን ዕቅድ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል።

ዛሬ ለመመረቅ የበቁትን 450 ሞግዚቶች ያሰለጠነው ‘እሹሩሩ’ የስልጠና ማዕከል ሲሆን ከመካከላቸው 50 የኤርትራ ስደተኞች ይገኙበታል፤ ቀሪዎቹ ከአረብ አገራት ተመላሽ የሆኑ ስራ አጥ ሴቶች ናቸው።

ስልጠናው ሳይንሳዊ የህጻናት አስተዳደግ ክህሎትን የተላበሰ በመሆኑ ምሩቃኑ በዘርፉ ብቃት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚችሉ እንደሆነ የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አብራርተዋል።

ለበርካታ ዓመታት በአረብ አገር በስደት የቆዩት ወጣት መሰረት ሸዋዬና ብሩክታዊት ወልዴ በሰጡት አስተያየት ህጻናትን በማሳደግ ዘርፍ ሙያ ከማካበታቸው ባሻገር በዘርፉ የሥራ እድል ባለቤት በመሆናቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል።

የክህሎት ስልጠና በመስጠት ተግባር የተሰማራው እሹሩሩ የስልጠና ማዕከል ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሙሉጌታ በበኩላቸው በተለይ የህፃናት አስተዳደግና እንክብካቤ ዘርፍ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እንዲመራ የበኩሉን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ሰልጣኞቹ ከሚያገኙት የስራ ዕድል ባሻገር ጥሩ ዜጋና በስብዕና የታነጸ ትውልድ ለማፍራት ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።

እሹሩሩ የስልጠና ማዕከል ስልጠናውን የሚሰጠው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ከሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ነው።