ኢትዮጵያ ከኳታር ጋር ያላትን የትብብር መስኮች የማስፋት ፍላጎት አላት

64
ነሐሴ 14/2011 ኢትዮጵያ ከኳታር ጋር ያላትን የትብብር መስኮች የማስፋት ፍላጎት እንዳላት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ። ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የኳታር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ መሐመድ ቢን አብዱልራህማን አል-ታኒን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። ኢትዮጵያና ኳታር በፖለቲካ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች ጠንካራ የሚባል ግንኙነት ያላቸው ሲሆን በተለያዩ መስኮች በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነዶች መፈራረማቸውም ይታወቃል። ኢትዮጵያም ከኳታር ጋር ያላትን የግንኙነት መስኮች የማስፋት ፍላጎት አሳይታለች። ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከሼክ መሀመድ ቢን አብዱልራህማን አል-ታኒን በነበራቸው ውይይት ኢትዮጵያ ከኳታር ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት ለማሳደግ በትምህርት፣ የመካለለኛ አመራር ደረጃን የማሳደግ ስልጠና እና የሴቶችን ሁለንተናዊ አቅም በማጎልበት ረገድ በትብብር መስራት እንደምትፈልግ መግለጻቸውን ከፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የኳታር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሀመድ ቢን አብዱልራህማን አል-ታኒ በበኩላቸው በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ዘርፈ ብዙ መሆኑን ገልጸዋል። በቀጣይም ያለውን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ለማጠናከር በትምህርት፣ በጤና እና በልዩ ልዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት አገራቸው ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል፡፡ ሚኒስትሩ አያይዘውም ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም መረጋገጥ እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ አድንቀው በተለይ በቅርቡ በሱዳን መረጋጋትና በሰላማዊ የስልጣን ክፍፍሉ ላይ የነበራትን ሚና ልዩ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የኳታር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ መሀመድ ቢን አብዱልራህማን አል-ታኒ ትናንት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸው የሚታወስ ነው። ሁለቱ ወገኖች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጋቢት ወር 2011 በኳታር ይፋዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት የተጀመረውን ውይይት በማስቀጠል በቁልፍ የሁለትዮሽ ትብብር ጉዳዮች ላይ ተነጋግረዋል፡፡ ሼክ መሐመድ ከዚህ ቀደም ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች በተለይም በሆቴል፣ ስኳር ፋብሪካ፣ በቱሪዝም ልማትና አዳዲስ የኩላሊት ሕክምና ማዕከላት ግንባታን ለማስጀመር ዝግጁነት እንዳለ መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡ ኢትዮጵያና ኳታር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1995 የጀመሩ ቢሆንም በ2008 ዓ.ም መቋረጡ ይታወሳል። ለግንኙነታቸው መቋረጥ ምክንያቱ ደግሞ የኳታር መገናኛ ብዙኃን በተለይም አልጀዚራ አሸባሪ ተብለው የተሰየሙ ድርጅቶችን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እንደሚደግፍ ኢትዮጵያ ይፋ ማድረጓ ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት ድርጊቱን በመቃወም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ እንዲቋረጥ አድርጓል። የኳታሩ ኤሚር ሼክ ሀማድ ቢን ካሊፋ አል ታኒ ከአራት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ያደረጉት ይፋዊ ጉብኝት ግን ሁለቱ አገራት ግንኙነታቸውን ዳግም እንዲያድሱ በር የከፈተ ሆኗል። ይህም በመሆኑ አገሮቹ ተደጋጋሚ ቀረጥ በማስቀረት፣ በአየር ትራንስፖርት፣ በኢንቨስትመንት፣ በባህል እና ንግድ ላይ ተባብረው ለመስራት 11 የመግባቢያ ስምምነቶችን እንድፈራረሙ አስችሏቸዋል። የሁለቱ አገራት መሪያዎች በተለያዩ ጊዜያት በየአገራቱ የሚያደርጉት ጉብኝት የአገራቱን የሁለትዮሸ ግንኙነት ይበልጥ እያጠናከር መጥቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም