የቤኒሻንጉል ጉሙዝና ኦሮሚያ ክልሎች ስምምነቶችን ተፈራረሙ

119
አሶሳ ነሐሴ 14 ቀን 2011 በምዕራብ ኢትዮጵያ አራት ክልሎች የጋራ መድረክ በሁለት ክልሎች መካከል ተጨማሪ ስምምነቶች ተፈረመ፡፡ የኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አማራና ጋምቤላ ክልሎች በአሶሳ ከተማ ለሁለት ቀናት ያካሄዱት የሠላምና የልማት የጋራ መድረክ ዛሬ ተጠናቋል፡፡ በመድረኩ ማጠቃለያ ተጨማሪ ስምምነቶችን የተፈራረሙት የኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ናቸው፡፡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሠላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አየለ እንደገለጹት ስምምነቱን የተፈራረሙት በክልሎቹ የሚገኙ 23 ወረዳዎች ናቸው። በዚህም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአሶሳና ካማሽ ዞኖች ስር የሚገኙ ሰባት ወረዳዎች ፈርመዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ደግሞ በምዕራብ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋና ቄለም ወለጋ ዞኖች የሚገኙ 16 ተጎራባች ወረዳዎች ስምምነቱን ተፈራርመዋል ብለዋል፡፡ ስምምነቱ በክልሎቹ ደረጃ  የተከናወኑትን የሠላምና የልማት ተግባራት በዞንና በወረዳ ደረጃ ለማውረድ እንደሚያስችሉ አስረድተዋል፡፡ በመድረኩ የምዕራብ የአገሪቱ የሚገኙ ክልሎች ሕዝቦች የጋራ እሴቶችና ፌደራሊዝም እንዲሁም የሕዝብ ለሕዝብና ክልላዊ መንግሥታትን ግንኙነት የሚያጠናክሩ ጥናታዊ ጸሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ የህዝቦችን አንድነት በሚፈታተኑና ለውጡን የሚያደናቅፉ ችግሮች መከላከል በሚቻልባቸው መንገዶች ውይይት ተደርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም