የመንግስታቱ ድርጅት በሰብአዊ ተግባር ጉልህ አስተዋፆ ላደረጉ ሴቶች አድናቆቱን ገለጸ

77
አዲስ አበባ ኢዜአ ነሀሴ 14/2011  በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ተጠሪ ኤኒያስ ቹማ በሰብአዊ ተግባር ጉልህ አስተዋፆ ላደረጉ ሴቶች አድናቆታቸውን ገለጹ። 10ኛው ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ቀን "ሴት ሰብአውያን" በሚል መሪ ሃሳብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከብሯል። በአዲስ አበባም እለቱ በኢትዮጵያ ለተፈናቀሉ ዜጎች የሰብአዊ እርዳታ ሲሰጡ የነበሩ ሴቶችን በማሰብ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል። በኢትዮጵያ የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ተጠሪ ሚስተር ኤኒያስ ቹማ የዘንድሮው ዓለም አቀፍ ሰብአዊነት ቀን ሲከበር ሴት ሰብአውያን መስዋዕትነት በመክፈል ራስ ወዳድ ሳይሆኑ ያደረጉትን አስተዋጽኦ በማሰብ መሆኑን ገልጸዋል። እለቱ በኢትዮጵያ ሲከበር ተፈናቃዮችን ተቀብለው ባስተናገዱ ማህበረሰቦች ውስጥ ሴቶች ያደረጉትን ሰብአዊነት የተሞላበት ተግባር እውቅና መስጠት ይገባል ብለዋል። ኢትዮጵያን እርዳታ በፈለጉበት ወቅት ሴቶች ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን ከማንም ቀድመው እርዳታ ማድረጋቸውን ጠቅሰው ለዚህም አድናቆታቸውን ገልጸዋል። እ.አ.አ በ2018 የመፈናቀል ቀውስ በከፋበት ወቅት ጀግና እና ለጋስ የኢትዮጵያ ሴቶች የበኩላቸውን ድጋፍ አድርገዋልም ነው ያሉት። ምግብና ውሃ በማካፈል፣ መለጠያ በመስጠት ያላቸውን ነገር ሁሉ በሰብአዊነት በማካፈል አለኝታ መሆናቸውንም አመልክተዋል። በመሆኑም የሃብት የቁሳቁስ ውስንነት ሳይበግራቸው ያላቸውን በመለገስ ለጋስነታቸውን ያስመሰከሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች መኖራቸውን ቹማ ጠቅሰዋል። "ምንም መደበኛ ገቢ እንኳን ባይኖረኝም ያለኝን ሰጥቻለሁ ወገኖቼ ውጪ እየተሰቃዩ እንዴት እኔ ቤቴ እቀመጣለሁ" በማለት ከድጋፍ አድራጊ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች መካከል እንደገለጹላቸውም አስታውሰዋል። "አጋጣሚ ሆኖ እንጂ ከተፈናቀሉት አንዷ ልሆን እችል ነበር ብዬ በማሰብ ድጋፍ ለማድርግ ተነሳሳሁ" በማለት በወቅቱ ሰብአዊ ድጋፍ ስታደርግ ያገኟትን ሌላ ሴትም አንስተዋል። በወቅቱ በእድሜ የገፉ ሰዎች፣ ህጻናትና ነፍሰ ጡሮች ተፈናቅለው በማየታቸው ማዘናቸውን የገለፁት ኤኒያስ ቹማ ሰብአዊ ተግባር በፈጸሙ ሰዎችም መደሰታቸውን ተናግረዋል። እነዚህንና ሌሎች በርካታ ጀግና ሰብአውያን ክብር እንደሚገባቸው ገልጸው ያም ቢሆን ያበረከቱት አስተዋጽኦ በበቂ ሁኔታ እውቅና እንዳልተሰጠውም ያምናሉ። በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ለተጎዱ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዜጎች ድጋፍ ለሚያደርጉ አካላትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል። መንግስት ለዜጎች መፈናቀል ምክንያት የሆኑ መንስኤዎችን በመለየት መፍትሄ በመስጠት እንዲሁም ዜጎች እንዳይፈናቀሉ ሰላምና መረጋጋት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል። የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘይኑ ጀማል በበኩላቸው የኢትዮጵያ ሴቶች የተፈናቀሉ ዜጎችን በጥረታቸውና ባላቸው ሀብት በማገዝ ሰብአዊነታቸውን በተግባራቸው አሳይተዋል ብለዋል። በዚህ ሰብአዊ አስተዋፆ ለተሳተፉ ሴቶች በሙሉ ከፍተኛ አክብሮት እንዳላቸው በመግለፅ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉትዬሬዝ ቀኑን አስመልክቶ በቪድዮ ያስተላለፉትን መልእክት ለታዳሚዎች ቀርቧል። የተመድ የሰብአ ዊጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) ቀኑን አስመልክቶ በኢትዮጵያ የሰራው ዶክመንተሪ ፊልምም በታዳሚያን ታይቷል። የተመድ የስራ ሃላፊዎችና የሰብአዊ ጉዳይ አስተባባሪዎች፣ የተለያዩ አገራት ኤምባሲ ተወካዮችና የልማት አጋሮች በኢትዮጵያ በተከበረው የዓለም የሰብአዊነት ቀን ላይ ተሳትፈዋል። የዓለም የሰብአዊነት ቀን እ.አ.አ ከ2009 ጀምሮ በመከበር ላይ ይገኛል። የአከባበሩ መነሻ እ.አ.አ በ2003 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና መቀመጫ በሆነችው ባግዳድ በደረሰ የቦምብ ፍንዳታ 22 የተመድ የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞች መገደላቸውን ተከትሎ ነው። ስዊድን እ.አ.አ በ2009 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት 64ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የውሳኔ ሀሳብ አቅርባ ጉባኤው 22 ሰዎች የሞቱበት ቀን እንዲታሰቡ ለማድረግ ነሐሴ 14 ቀን 2011 ዓ.ም የዓለም የሰብአዊነት ቀን እንዲሆን ወስኗል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም