የመቀሌ ከተማ ሴቶች የአሸንዳ በዓልን ምክንያት በማድረግ ችግኝ ተከሉ

105

መቀሌ ነሐሴ 14 ቀን 2011 የመቀሌ ከተማ ሴቶች የአሸንዳ በዓልን ምክንያት በማድረግ ዛሬ በሰማዕታት ሐውልት ግቢ ችግኝ ተከሉ።
ሴቶቹ ችግኞቹን የተከሉት በዓሉን ከማድመቅ በተጨማሪ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የአረንጓዴ ልማት ፕሮግራምን ለማሳካት እንደሆነም ተገልጿል።

ሴቶቹ ችግኞቹን ተንከባክበው ለማጽደቅ እንደሚሰሩም ተገልጿል።

በተከላው ከተሳተፉት ሴቶች መካከል ወይዘሮ ፅጌ አብርሃ የሴቶች የነጻነት መገለጫ የሆነውን በዓል ለማድመቅና መነሳሳትን ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል።

እንዲሁም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የጀመሩትን የአረንጓዴ ልማት ፕሮግራም ከዳር እንደሚያደርሱ ተናግረዋል።

ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ኮማንደር አበባ ነጋሽ በበኩላቸው በችግኝ ተከላው የተሳተፉት በአረንጓዴ ልማት መርሐ ግብር  ስኬት ተሳትፏቸውን  ለማረጋገጥ መሆኑን ገልጸዋል።

ሴቶች በሁሉም መስኮች ከተሰማሩ የማያሳኩት ሥራ እንደሌለ ለማሳየትና በዓሉን ለማድመቅ ነው ብለዋል።

የትግራይ ክልል ሴቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር የትምወርቅ ገብረመስቀል እንዳሉትም ችግኝ ተከላው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለአረንጓዴ ልማት ፕሮግራም ስኬት የነበራቸውን ታላቅ አስተዋጽኦ ለማስታወስ የተዘጋጀ ነው።