የደቡብ ክልል ሕዝቦችን አንድነት ለማጠናከርና አገራዊውን ለውጥ ለማራመድ ተዘጋጅተናል- የሐድያ ዞን አመራሮች

62
ሆሳእና ነሐሴ 14 /2011የደቡብ ክልል ሕዝቦችን አንድነት ለማጠናከርና አገራዊውን ለውጥ ለማራመድ ዝግጁ መሆናቸው የሐድያ ዞን አመራሮች አረጋገጡ። በዞኑ ''ኅብረ ብሄራዊ አንድነታችን ለጋራ እድገታችንና ለተደማጭነታችን መሠረት ነው!'' በሚል መሪ ቃል የተካሄደው የአመራሮች መድረክ ትናንት ተጠናቋል፡፡ አመራሮቹ በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ እንዳመለከቱት የክልሉ  ሕዝቦችን  አንድነት ለማጎልበትና በአገሪቱ የተጀመረው ለውጥ ስኬታማነትና ለለውጡ ተግባራዊነት ሕዝብን ያንቀሳቀሳሉ። የዞኑን ሕዝብ ከአጎራባች ሕዝቦች ጋር ተቻችሎ የመኖር እሴቱንና አንድነቱን ጠብቆ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል። ለውጡን ተከትሎ መደበኛ ባልሆነ መንገድ በመደራጀት የሕዝብ ጥያቄዎችን ሽፋን በማድረግ ሥርዓተ አልበኝነትን ለማንገስ የሚንቀሳቀሱ አካላትን በመታገል ለሰላምና ልማት መረጋገጥ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል። በክልሉ ባለፉት 28 ዓመታት በኢኮኖሚያዊ ፣ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሂደቶች አመርቂ ውጤት መመዝገባቸውንና ዴሞክራሲያዊና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መገንባቱን አስረድተዋል፡፡ ቢሆንም የአገሪቱ የለውጥ፣የልማትና ዴሞክራሲያዊ ሂደት ግንባታ የሚያደናቅፉ ክስተቶች ለዜጎች መፈናቀል ለሕይወትና ንብረት መጥፋት ምክንያት መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡ ለጥፋቱ ዋናው ተዋናይ የአመራር ሥነ ምግባር ጥሰት፣ የጎሳ መደበላለቅ፣ ሕዝበኝነትና ብሄርተኝነት አዝማሚያዎች ማቆጥቆጥ  እንደሆነ ያመለከቱት አመራሮቹ፣በዚህም ተቋማዊ ባህርይው እየተጎዳ የመጣውን ድርጅት የሚያጠናክሩ ሥራዎች መከናወን እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ የከተሞች መሬትና ጎሰኝነትን መሠረት ያደረጉ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከቶችን እንደሚመክቱ አስታውቀዋል። በደቡብ ክልል የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ደኢሕዴን) ባስጠናው የአደረጃጀት ጥናትና በወቅታዊ አገራዊና ክልላዊ ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ የአመራሮች መድረክ በዞኖች ደረጃ ሰሞኑን ሲካሄድ ቆይቷል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም