በሐረሪ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ከ9ሺህ በላይ ወጣቶች ሥራ ይይዛሉ

118

ሐረር ነሐሴ 13 / 2011 በሐረሪ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ከ9ሺህ በላይ ወጣቶች ሥራ እንደሚይዙ የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ገለጸ።
ከብድር አሰጣጥ ጋር ያሉ ችግሮች ትኩረት እንዲሰጣቸው ወጣቶች ጠይቀዋል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አብዱልሃኪም አብዱማሊክ ለኢዜአ እንደገለጹት በሐረር ከተማና  በገጠር  ቀበሌዎች  ለሚገኙ ወጣቶች ሥራ ይፈጠራል።

በተለይ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ለተመረቁና ተመርቀው ያለ ሥራ  የተቀመጡ  ወጣቶችን በከተማ ግብርና፣ በኮንስትራክሽን፣ በማኑፋክቸሪንግና በሌሎች  ሥራዎች    ለማሰማራት መታቀዱን ተናግረዋል።

እንዲሁም ተመራቂዎቹ በክልሉ ቢሮዎች እንዲሁም በክልሉ ኢንቨስትመንት ከተሰማሩ ባለሀብቶች ጋር በመቀናጀት  ሥራ እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።

“የክልሉ መንግሥት ዘንድሮ በመደበው 150 ሚሊዮን ብር ለወጣቱ  ብድር በመስጠት  የሥራ  ዕድል ባለቤት  ከማድረግ ጎን ለጎን የስልጠናና  የገበያ ትስስር  ይፈጠራል” ብለዋል።

የብድር አገልግሎት በአንድ ማዕከል የሚሰጥበት አሰራር መዘርጋቱንም ገልጸዋል።

”በከተማ ግብርና ሥራ ፈጥሮ መንቀሳቀስ ዕቅዴ ነው”ያለው በግብርና ሙያ በመጀመሪያ ዲግሪ የያዘው ተማሪ አብርሃም እንግዳ፣ ወደ ሥራ ለመግባት በአሰራር ላይ የሚታዩ ችግሮች እንዲስተካከሉ ጠይቋል።

ሌላው ተመራቂ ተማሪ  ደሜ ታደሰ እንደሚገልጸው ተመራቂዎች የመንግሥትን ሥራ ከመጠበቅ ሥራ ፈጥሮ መንቀሳቀስ የሚችልበት ስልጠና ማግኘቱን ገልጾ፣ተደራጅቶና ፈቃድ አውጥቶ ለመስራት ከብድር አሰጣጥ ጋር የሚታዩ ችግሮች መስተካከል አለባቸው ብሏል።

በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ4ሺህ በላይ  ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ ሥራ ማግኘታቸው ይታወሳል።