በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለመፍጠር በየተቋማቱ የአካዳሚክ ነፃነት ሊኖር ይገባል – ምሁራን

161

ነሀሴ 13/2011 በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለመፍጠር በየተቋማቱ የአካዳሚክ ነፃነት ሊኖር እንደሚገባ ምሁራን አሳሰቡ። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ ከዚህ በኋላ ሁሉም አካላት ተጠያቂ የሚሆኑበት አሰራር ተግባራዊ አደርጋለሁ ብሏል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባል ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ እንዳሉት፤ መንግስት በተማሪዎች ህብረት ስም ለፖለቲካ ጥቅም የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ማቆም አለበት።

በዩኒቨርሲቲዎች ያሉ የተማሪዎች ህብረት የሚባሉ ማህበራት በቡድን ተድራጅተው ተማሪዎችን እርስ በእርስ ሲያጋጩ እንጂ መፍትሄ ሲያመጡ አላየንም ብለዋል ፕሮፌሰሩ።

“በዩኒቨርሲቲዎች ሰላም ስለመደፍረሱ መስማት ያሳፍራል” ያሉት ፕሮፌሰር በየነ፤ መንግስትም ለተማሪዎች የአካዳሚክ ነጻነት ሊሰጣቸው ይገባል ነው ያሉት።

የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ፍጹም አሰፋ በበኩላቸው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለመፍጠር የአካባቢው ማኅበረሰብ ሚናው የጎላ እንደሆነ ማስገንዘብ ይገባል ብለዋል።

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ተወካይ ፕሮፌሰር አክሊሉ አዛዥ በተማሪዎች መካከል ሰላም እንዲሰፍን በተለያዩ አደረጃጀቶች ማሳተፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ተማሪዎችን በትምህርትና በተለያዩ አደረጃጀቶች እንዲሁም በክበባትና ሌሎች መንገዶች ማሳተፍ ከተቻለ ለሁከትና ብጥብጥ የሚሆን ጊዜ አይኖራቸውም ብለዋል።

የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር አረጋ ይርዳው  ሰላም ለመፍጠር ከባለደርሻ አካላት ጋር ከመስራት ባለፈ ሌሎችም አማራጮችን ማየት ይገባል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አማካሪ ዶክተር አለማየሁ ከበደ እንደሚሉት ደግሞ ከሚቀጥለው 2012 የትምህርት ዘመን ጀምሮ በየደረጃው ሁሉም ተጠያቂ የሚሆንበት አሰራር ይኖራል።