በወላይታ ሶዶ ከተማ የመሬት ናዳ የእናትና ልጅ ሕይወት ጠፋ

169

ሶዶ ነሐሴ 13 /2011  የከተማዋ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ወጋየሁ ዳና ለኢዜአ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው እናትና ልጅ ከምንጭ ውሃ ለመቅዳት በሄዱበት በተከሰተ ናዳ ሕይወታቸው አልፏል።

አደጋው የተከሰተው ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ገደማ በከተማው ድል በትግል ቀበሌ ሆርባቢቾ መንደር እንደነበርም አስረድተዋል።

የአደጋው ተጎጂዎች ያሰሙትን ጥሪ ተከትሎ ፖሊስና የአካባቢው ማህበረሰብ ሟቾችን ለማትረፍ ጥረት አድርጎ እንደነበር ገልጸዋል።

የሟቾቹ አስከሬን ለቤተሰቦቻቸው መሰጠቱንም አዛዡ ተናግረዋል።

ማህበረሰቡ በተለይም ከፍተኛ ዝናብ የሚጥልበትን ወቅት በመለየት ጥንቃቄ እንዲያደርግ ኢንስፔክተር ወጋየሁ አሳስበዋል።

በወላይታ ዞን ኦፋና ኪንዶ ኮይሻ ወረዳዎች ሰሞኑን በተከሰቱ አደጋዎች በሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል።