ሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለ500 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

62

ሃዋሳ (ኢዜአ) ነሀሴ 13 ቀን 2011- ሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በስሩ ካሉ ኩባንያዎች ጋር በመተባበር ለ500 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
የቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገላቸው የልማት ተነሺ ቤተሰብ ልጆች ሲሆኑ በእዚህም ቦርሳ፣ ደብተር እና የጽህፈት መሳሪያዎች ተበርክቶላቸዋል።

ለወላጆችም ለትምህርት ቤት ማስመዝገቢያና ለተጓዳኝ ወጪዎች የሚሆን የገንዘብ ስጦታ መሰጠቱን ነው የገለጸው።

የፓርኩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍፁም ከተማ እንዳሉት ድጋፉ ለ500 ተማሪዎች የተደረገ ሲሆን ባጠቃላይ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪም ወጥቶበታል ፡፡

ድጋፉ የተሰበሰበው ከኢንዱስትሪ ፓርኩ እና በውስጡ ከሚገኙ ኩባንያዎች መሆኑን ጠቁመው፣ ባለፈው ዓመትም በተመሳሳይ ለ450 ተማሪዎች ድጋፍ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ለኢንዱስትሪ ፓርኩ ዕውን መሆን የተነሺዎች አስተዋፅኦ የጎላ መሆኑን ያስታወሱት ሥራ አስኪያጁ “ድጋፉ አብሮነትን ከማጠንከር ባለፈ በማንኛውም የልማት ሥራ መሳተፍ እንደምንችል ያሳያል” ብለዋል።

እንደ አቶ ፍፁም ገለጻ በአሁን ወቅት በኢንዱስትሪ ፓርኩ 21 ኩባንያዎች በሥራ ላይ የሚገኙ ሲሆን ከ27 ሺህ በላይ ወጣቶችም የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ፡፡

የሥራ ዕድል ፈጠራውን ለማሳደግም ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል ፡፡

“ከትምህርት መሳሪያ ድጋፍ ባሻገር የልማት ተነሺ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች ቀጣይነት ባለው መልኩ ይከናወናሉ” ብለዋል፡፡

በአሁን ወቅት የእነዚህ ቤተሰቦች ልጆች ፓርኩ በፈጠራቸው የሥራ ዕድሎች ቅድሚያ አግኝተው ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉም ገልፀዋል ፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኦፕሬሽን እና ማኔጅመንት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ሰለሞን ድጋፉ በትምህርት ቁሳቁስ ብቻ ማቆም እንደሌለበት ተናግረዋል።

“ድጋፉ ለኢንዱስትሪ ፓርኩ ግንባታ ከአካባቢያቸው የተነሱ ዜጎች በሙሉ የተሻለ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሥራ መስራት እንደሚጠብቅብን ያመላክታል” ብለዋል ፡፡

የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክና በውስጡ ያሉ ኩባንያዎች ለልማት ተነሺ ቤተሰቦች ያሳዩት አጋርነትም አርአያነት ያለው አኩሪ ተግባር መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከተማ ዶባ በበኩላቸው “ኢንዱስትሪ ፓርኩ የከተማዋም የሀገርም ሀብት በመሆኑ ጠቀሜታውን ለማሳደግ በጋራ መንከባከብና መጠበቅ ይገባል” ብለዋል ፡፡

ድጋፉ ከተደረገላቸው የልማት ተነሺ ቤተሰቦች መካከል የስምንት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ አስናቀች ኢጃጆ በተደረገላቸው ድጋፍ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደሩ በመሆኑ የተረከቡት የትምህርት ቁሳቁስ ልጆቻቸውን ለማስተማር ከፍተኛ እገዛ እንዳለው አስረድተዋል ፡፡

ድጋፉን ላበረከቱላቸው አካላትም ምስጋናቸውን ገልፀዋል ፡፡

የሰባተኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ምትኩ ታምራት በበኩሉ የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ በማግኘቱ መደሰቱን ገልፆ በቀጣይ ትምህርቱን በርትቶ በመማር ወገኑንና አገሩን ለማገልግል እንደሚሰራ ተናግሯል ፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኩ የልማት ተነሺ ቤተሰቦች ከማህበረሰቡ ጋር በጋር በመሆን በፓርኩ ቅጥር ግቢ ውስጥ የችግኝ ተከላ ሥራ አከናውነዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡