በአፋር ከማዕድን ሀብት ህብረተሰቡንና ክልሉን ተጠቃሚ ለማድረግ ድጋፍ ይደረጋል…ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ

114

ሰመራ (ኢዜአ) ነሀሴ 13 /2011   በአፋር ክልል ከሚገኘው የማዕድን ሀብት ህብረተሰቡና ክልሉን የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርግ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ገለጸ።

በክልሉ ህገ-ወጥ የማዕድን ግብይትን መቆጣጠር ላይ ያተኮረና የወረዳና ክልል ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ዛሬ በሰመራ ከተማ ተካሄዷል።

በመድረኩ መዝጊያ ላይ የተገኙት የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ እንደተናገሩት በሀገሪቱ የተጀመረው ፖለቲካዊ ሪፎርም በኢኮኖሚው መስክ እንዲደገም የማዕድን ዘርፉ የውጭ ምንዛሬን በማስገኘትና የስራ-አድል በመፍጠር ድርሻው የጎላ ነው።

ይሁንና በተለያዩ አካባቢዎች የሚሰተዋለው ህገወጥ የማዕድን ንግድ ዘርፉ  ድርሻውን በአግባቡ እንዳይወጣ በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች አመራሩ እራሱ በህገወጥ እንቅስቃሴው ላይ ተሳታፊ ስለሆነ ህገ-ወጥነትን ለመቆጣጠር ለሚደረጉ ጥረቶች እንቅፋት የሚሆንበት አጋጣሚ መኖሩንም አመልክተዋል።

ችግሩን በመፍታት መንግስትና ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ ግልጽነት የተሞላበት አሰራር በመዘርጋት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

“በተጨማሪም በዘርፉ ከምርት እስከ ግብይት ድረስ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፋታት መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው” ብለዋል።

በአፋር ክልል በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች በቀጣይ መሰል ችግሮች እንዳይገጥሙ በትኩረትና በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ዶክተር ሳሙኤል አሳስበዋል።

“ክልሉ ወርቅና ኦፓልን ጨምሮ ሰባት የተለያዩ የማዕድን ሀብቶች ባለቤት ቢሆንም ዘርፉ ለህገ-ወጥነት የተጋለጠ በመሆኑ ህብረተሰቡም ሆነ ክልሉ ተገቢውን ጥቅም እያገኙ አይደሉም” ብለዋል።

በቀጣይ ክልሉ በዘርፉ ለወጣቶች ሥራ እድል እንዲፈጥር፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጥና ለውጭ ምንዛሬ መገኘት አስተዋጽኦ እንዲያበረክት በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

ለእዚህም ሚኒስቴር መስሪያቤቱ የግብይት ማዕከሎችን በአቅራቢያው ከመክፈት ባለፈ ለክልሉ የቴክኖሎጂ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ነው የገለጹት።

የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው ክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት ለ57ሺህ ወጣቶች የሥራ አድል ለመፍጠር እየሰራ መሆኑንና ከዚህ ውስጥ በማዕድን ዘርፍ ለ3ሺህ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል።

“በክልሉ በባህላዊ መንገድ የሚለሙ የተለያዩ የማዕድን ሃብቶችን በቅርበት የሚገዛ የግብይት ማዕከልም ሆነ ለስራው አጋዥ የሆኑ የቴክኖሎጂ ድጋፍ የሚያደርግ አካል ባለመኖሩ ዘርፉ ለህገ-ወጦችና ጥገኛ አመራሮች ተጋልጧል” ብለዋል።

በመሆኑም ዘርፉን  ከህገወጦች ለመከላከልና በሀብቱ ህብረተሰቡና ክልሉ ይብልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

የአፋር ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገዶ ሀሞሎ በበኩላቸው በክልሉ የተለያዩ የማዕድን ሃብቶች ቢኖሩም የክልሉን ህዝብ በተወሰነ ደረጃ ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለው ከጨው ሃብቱ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል።

“በቀጣይ ወርቅን ጨምሮ በተለያዩ የማዕድን ሃብት ልማት ዘርፍ ወጣቶች ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይሰራል” ብለዋል።

ለእዚህም ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ሆነ ከሚመለከታቸው የክልልና የፌዴራል ባለድርሻ አካላት ጋር የተጀመረውን ቅንጅታዊ አሰረር በማጠናከር እንደሚሰራ ነው የተናገሩት።

ለግማሽ ቀን በተካሄደው ውይይት  ከ9 ወረዳዎችና የዞን እንዲ ሁም የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል ።