በማዕከላዊ ጎንደር 50ሺ የሚጠጉ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለማምጣት ዝግጅት ተጀመረ

66

ነሐሴ 13 / 2011 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ባለፈው ዓመት ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ትምህርታቸውን አቋርጠው የቆዩ 50ሺ የሚጠጉ ተማሪዎችን በ2012 የስራ ዘመን ወደ ትምህርት ገበታ ለማምጣት ዝግጅት መጀመሩ ተገለጸ፡፡፡
የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን እርካቤ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት በግጭቱ ወቅት 94 የመጀመሪያና 52ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ቆይተዋል፡፡

በዚህም በትምህርት ቤቶቹ ይማሩ የነበሩ 50ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለማቋረጥ መገደዳቸውን ጠቁመው ከ3ሺ በላይ መምህራንም ከስራ ገበታቸው መለየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

ተማሪዎቹ ያቋረጡትን ትምህርት መስከረም 2012 ዓ.ም ለማስጀመር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን የሚያጠናክር የእርቀ ሰላም መድረኮች ከአካባቢ አስተዳደሮች ጋር በመቀናጀት መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከእነዚህ ተማሪዎች መካከልም ከ10ሺ በላይ ተማሪዎች በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፕሮግራም የክረምት ትምህርት መርሃ ግብር እንዲከታታሉ በመደረግ ላይ ነው።

በግጭቱ ወቅት በቃጠሎ ጉዳት የደረሰባቸውን አራት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ዳግም ወደ ስራ ለማስገባት በተደረገው ርብርብ የገለድባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ተጠግኖ ለአገልግሎት ዝግጁ ተደርጓል፡፡

በመፋጠን ላይ የሚገኙት የቀሪዎቹ ሶስት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጥገና ተጠናቀው ስራ ሲጀምሩም ከ2ሺ በላይ ተማሪዎችን በመጪው መስከረም ወር ተቀብለው እንደሚያስተናግዱ ኃላፊው ገልጸዋል።

ከመስከረም 6 ቀን 2011ዓ.ም ለአምስት ቀናት ትምህርት አቋርጠው የቆዩ ተማሪዎች በአዲስ መልክ ምዝገባ በማካሄድ ትምህርቱን የማስጀመር ስራ እንደሚከናወን አስረድተዋል፡፡

ለትምህርት ቤቶቹ የመማር ማስተማር ስራ የሚያስፈልጉ የትምህርት መርጃ ግብአቶች የማሟላት ስራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

በሌላም በኩል በ2012 የትምህርት ዘመን በዞኑ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ከ80ሺ በላይ ህጻናትን ወደ ትምህርት ገበታ ለማምጣት በመጪው መስከረም የቤት ለቤት ቅስቀሳና ምዝገባ ይካሄዳል ተብሏል፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በ2011 የትምህርት ዘመን በመጀመሪያ ፣በሁለተኛ ደረጃና በመሰናዶ ትምህርት ቤቶች ከግማሽ ሚሊዮን  በላይ ተማሪዎች መደበኛ ትምህርታቸውን መከታተላቸውን ከመምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡