የቂሊንጦ ቃጠሎ ተከሳሾች የቅጣት ማቅለያ እንደማያቀርቡ ገለጹ

537

ነሀሴ 13/2011 ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የቂሊንጦ የተከሳሾች ማቆያ ቃጠሎ ጋር በተያያዘ የተከሰሱ ግለሰቦች ለፍርድ ቤቱ የቅጣት ማቅለያ ሐሳብ እንደማያቀርቡ ገለጹ።

ተከሳሾቹ ለፍርድ ቤቱ የቅጣት ማቅለያ ሐሳብ እንደማያቀርቡና ጥፋተኛም እንዳልሆኑ ነው ያመለከቱት።

ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም ቂሊንጦ የተከሳሾች ማቆያን አቃጥለዋል ተብለው ክስ የተመሰረተባቸው አቶ ጌታቸር እሸቴ፣ አቶ ፍፁም ጌታቸው፣ አቶ ቶፊቅ ሽኩር እና አቶ ሸምሱ ሰይድ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

ተከሳሾቹ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት በተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የፍርድ ማቅለያ ካላቸው ለችሎቱ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ በመሰጠቱ ነው።

ነገር ግን ተከሳሾቹ በተከሰሱበት ጉዳይ ተጠያቂ ሊሆኑ እንደማይገባና ከማረሚያ ቤቱ ቃጠሎ ጋር በተያያዘ ክስ የተመሰረተባቸው ሌሎች አካላት በመኖራቸው ወንጀሉ እነሱን እንደማይመለከት ተናግረዋል።

ከቃጠሎው ጋር በተያያዘ የግንቦት ሰባት አባላትን ጨምሮ 159 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው የነበረ ቢሆንም በሂደት እንደተለቀቁ አመልክተዋል።

እነርሱ በጉዳዩ እጃቸው እንደሌለበትና ነፃ እንደሆኑ በማብራራትም ለፍርድ ቤቱ የክስ ማቅለያ እንደማያቀርቡ ገልጸዋል።

ፍርድ ቤቱም ውሳኔውን የሰጠው በዓቃቤ ሕግ የቀረበለትን የሰውና የሰነድ ማስረጃ በጥልቀት መርምሮ በመሆኑ ተከሳሾች በሚሰጣቸው ውሳኔ ላይ በየደረጃው ይግባኝ የመጠየቅ መብታቸው የተጠበቀ መሆኑን አስረድቷል።

ተከሳሾቹ የፍርድ ማቅለያ ለማስገባት የማይፈልጉ መሆናቸውን በተከላካይ ጠበቃቸው በኩል በፅሑፍ እንዲያስገቡም ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በክሱ ላይ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ለጥቅምት 7 ቀን 2012 ዓ.ም ቀጠሮ ተይዟል።