ጋዜጠኞች ከጥላቻ ንግግሮችና የሙያ ስነ-ምግባርን ከሚጥሱ ስራዎች መቆጠብ አለባቸው - ባለሙያዎች

65
ነሐሴ 13 / 2011ጋዜጠኞች ከጥላቻ ንግግሮችና የሙያ ስነ-ምግባርን ከሚጥሱ ስራዎች ተቆጥበውና ሙያቸውን አክብረው መስራት እንደሚገባቸው የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ተናገሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃንና በማህበራዊ ሚዲያዎች ሙያዊ ስነ-ምግባሩን በጣሰ መልኩ  የግለሰቦችንና የድርጅቶችን ስም እየጠቀሱ የተዛቡ መረጃዎችን ለህዝብ የሚያደርሱና የጥላቻ ንግግሮችንም የሚያሰራጩ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ተበራክተዋል። በተለይም የጋዜጠኝነት ሙያን እንደ ምሽግ በመጠቀም ብሔር፣ ኃይማኖትና ጾታን መሰረት በማድረግ የሀሰት መረጃና ጥላቻ ሃሳብን የያዙ ጽሁፎችና ፎቶዎች በተለያዩ ጊዜያት ያሰራጫሉ። ይህም በአገርም ሆነ በህዝብ ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽእኖ ከፍተኛ ስለመሆኑም ብዙዎች ይናገራሉ። ኢዜአ ያነጋገራቸው የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የሚሰሯቸው ስራዎች ስለሚያስከትሉት ጥቅምና ጉዳት ብሎም በአገርና በማህበረሰቡ ላይ ሊያሳድሩ ስለሚችሉት ተጽእኖ ቅድሚያ በማመዛዘን መስራት አለባቸው ይላሉ። የአዲስ አድማስ ጋዜጣ አርታኢ ወይዘሮ መታሰቢያ ካሳዬ እንደሚሉት "ጋዜጠኝነት በራሱ ትልቅ ስነ-ምግባርን የሚጠይቅ የሙያ ዘርፍ ነው"። በጋዜጠኝነት የሙያ ዘርፍ የሚሰሩ ስራዎች አገርን በመገንባትም ሆነ በማፍረስም ረገድ ትልቅ ድርሻ ያለው በመሆኑ የሚሰሯቸውን ስራዎች በጥንቃቄ መስራት አለባቸውም ብለዋል። በዚህም ጋዜጠኛው ሙያውን የሚያከብር፣ የሚሰራውን የሚያውቅና ለአገሩና ለህዝቡ የሚቆረቆር ባለሙያ መሆን አለበት ሲሉም ተናግረዋል። ጋዜጠኛ አቤል ዋበላ 'ከጉበና መንገድ ዲጂታል ሚዲያ' በበኩሉ "አብዛኛውን ጊዜ የጥላቻ ንግግሮችና የተዛቡ መረጃዎች የሚያሰራጩት ራስንና ሙያውን ካለማክበር የተነሳ ነው"። በመሆኑም ጋዜጠኛው ለራሱና ለሙያው ተገቢውን ክብር በመስጠት ሚዛናዊና ትክክለኛ በሆኑ ዘገባዎች መረጃዎችን ለህዝብ በማድረስ ረገድ ሃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት አለበት ብሏል። የሪፖርተር ጋዜጣ አርታኢ ጋዜጠኛ ብሩህ ይሁንበላይ በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ ከስነ-ምግባር ውጪ የሆኑ ስራዎችን የሚሰሩ ባለሙያዎች በቸልተኛነትና በግዴለሽነት በሚያደርጉት ተግባራት የሙያውን ስም ሲያጎድፉ ይስተዋላሉ። ይሁንና ሙያው ህዝብን መሰረት ያደረገና ለህዝብ ጥቅም የቆመ በመሆኑ የሙያ ስነ-ምግባርን የተላበሰ ሊሆን አንደሚገባውም ገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም