የ12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች የመክፈቻ ስነ ስርአት ዛሬ ምሽት ይካሄዳል

101

አዲስ አበባ ነሀሴ 13/2011  በሞሮኮ አስተናጋጅነት የሚካሄደው 12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች የመክፈቻ ስነ ስርአት ዛሬ ምሽት ይካሄዳል።

በሞሮኮ ርዕሰ መዲና ራባት፣ካዛብላንካ፣ኤል ጃዲዳና ኬሚሴት ከተሞች በሚካሄደው ውድድር በ26 የስፖርት አይነቶች ከ54ቱ አፍሪካ አገራት የተወጣጡ ከ7 ሺህ በላይ ስፖርተኞች የሚሳተፉ ሲሆን በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛ የስፖርት ልዑክ የሚሳተፍበት ይሆናል።

የአፍሪካ ጨዋታዎች የመክፈቻ ስነ ሰርአት 5 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው በልዑክ ሙላይ አብደላ ስታዲየም ከምሽቱ 3 ሰአት ከ45 ጀምሮ የሚከናወን ይሆናል።

በአፍሪካ ጨዋታዎች የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ትናንት ሞሮኮ የገባ ሲሆን በአገሪቷ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲም አቀባበል ተደርጎለታል።

በሞሮኮው የአፍሪካ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጨዋታዎች ተሳትፎዋ ታሪክ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስፖርተኛና የልዑካን ቡድን ታሳትፋለች።

በ13 የስፖርት አይነቶች 188 ስፖርተኞች የሚሳተፉ ሲሆን በአጠቃላይ ከ250 እስከ 270 የሚሆን ልዑካን ቡድን ወደ ስፍራው አቅንቷል።

ወርልድ ቴኳንዶ፣ አትሌቲክስ፣ ካራቴ፣ ቴኒስ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ቦክስ፣ ጅምናስቲክ፣ ብስክሌት፣ ውሃ ዋና፣ ባድሜንተን፣ ክብደት ማንሳት፣ ቼስና ቅርጫት ኳስ ኢትዮጵያ የምትሳተፍባቸው የስፖርት አይነቶች ናቸው።

ስፖርተኞቹ ላለፉት ሶስት ወራት ለአፍሪካ ጨዋታዎች ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ካራቴ ቅርጫት ኳስ እና ቼስ በሞሮኮው የአፍሪካ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ የምትሳተፍባቸው አዲስ የተጨመሩ የስፖርት አይነቶች ናቸው።

12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች (የአፍሪካ ኦሎምፒክ) የሚባለው ውድድር እ.አ.አ በ2020 በቶኪዮ ለሚካሄደው የኦሊምፒክ ውድድር ለመሳተፍ እንደ ማጣሪያ ውድድር የሚያገለግል ነው።

የአትሌቲክስ ውድድር ነሐሴ 20 ቀን 2011 ዓ.ም የሚጀምር በመሆኑ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድን ሐሙስ ነሐሴ 16 ቀን 2011 ዓ.ም ሞሮኮ እንደሚደረስም ለማወቅ ተችሏል።

የእግር ኳስ፣ የባህር ዳርቻ መረብ ኳስ እና የጁዶ ስፖርቶች የማጣሪያ ውድድሮች ከትናንት በስቲያ ጀምሮ መካሄድ የጀመሩ ሲሆን የሌሎች ስፖርት ማጣሪያዎች ከነገ ጀምሮ መካሄድ ይጀምራሉ።

በአፍሪካ ጨዋታዎች የመክፈቻ ስነ ስርአት የሞሮኮ ንጉስ ሞሀመድ አምስተኛ ይገኛሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም በስነ ስርአቱ ላይ ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የ12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።

የ13 የአፍሪካ ጨዋታዎች እ.አ.አ በ2023 በጋና አስተናጋጅነት የሚካሄድ ይሆናል።