የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ያስቀመጥኳቸውን ግቦች ያሳካሁበት ነበር አለ

71
ጅማ ነሐሴ 13 / 2011 የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ የተጠናቀቀው በጀት ዓመት ያስቀመጥኳቸውን ግቦች ያሳካበት እንደነበር ዋና ዳይሬክተሩ ገለጹ። በተያዘው በጀት ዓመት የኅብረት ሥራ ማህበራትን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ለመፍታት ትኩረት እሰጣለሁ ብሏል፡፡ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር ኤጀንሲው በጅማ ከተማ ከክልሎች ኅብረት ሥራ ማስፋፊያ ቢሮ አመራሮች ጋር ያካሄደውን ዓመታዊ ግምገማ ሲያጠናቅቅ ያለፈውን ዓመት''በአብዛኛው ለማሳካት ያስቀመጥናቸውን ግቦች አሳክተን ያለፈንበት የሥራ ዘመን'' ብለውታል፡፡ በተለይም የኅብረት ሥራ ማህበራት 25 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ካፒታል ማስመዝገባቸውን አንዱ ስኬት አድርገው አቅርበውታል፡፡ በአገር ውስጥ ግብይት 1ነጥብ 2 ሚሊዮን ቶን ምርቶችን በ4ሺ589 ማህበራት፣በ12 ዩኒዬኖችና በአንድ የኅብረት ሥራ ፌዴሬሽን ግብይት መፈጸሙን ጠቁመዋል፡፡ የገንዘብና ቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማህበራት ከ 17ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ በቁጠባና በካፒታል ማሰባሰባቸውንም አቶ ዑስማን አስታውቀዋል። በኅብረት ሥራ ማህበራት የተፈጠረው 634ሺ909 ሥራ አገራዊ አስተዋጽኦው 53 ነጥብ 3 በመቶ መድረሱን አመልክተዋል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት  በኦዲትና ኢንስፔክሽን እንዲሁም በብቃት ማረጋገጫ ንዑስ ዘርፎች ትኩረት በመስጠት የመሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማህበራት የፋይናንስ አቅርቦት በቂና ወቅቱን የጠበቀ ለማድረግ ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ወይዘሮ መናህል ኢምራን የፌዴራል መንግሥት የኤጀንሲውን የኦዲት ችግር ለማቃለል ድጋፍ እንደሚሻ ተናግረዋል፡፡ በተለይም የኦዲት ችግር ለመፍታት የሰው ኃይል ቁጥር አነስተኛ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የአቅም ውስንነት ይታያል ብለዋል፡፡ በማህበራቱ ያለው የፋይናንስ አቅርቦት የሚታየው ውስንነት ምርቶችን ወቅት ጠብቆ በመግዛት ለገበያ በማቅረብ ክፍተት መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡ የትግራይ ክልል የኅብረት ሥራ ኤጀንሲ የእቅድና ክትትል ዳይሬክተር አቶ መብራቱ እምባዬ ኤጀንሲው በቀጣይ ለኦዲት ሥራ ትኩረት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም ማህበራት ወደ አግሮ ፕሮሰሲንግና ወደ ግብርና መካናዜሽን ለመግባት የፋይናንስ አቅርቦት ችግር እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ በፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ የኅብረት ሥራ ግብይት ዳይሬክተር ወይዘሮ ይርጋለም እንየው እንደሚሉት ከኦሮሚያክልል በስተቀር ክልሎች የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ይታይባቸዋል፡፡ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የክልሉን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር በመፍታቱ ውጤታማ አድርጎታል ብለዋል፡፡ በቀጣይ ዓመትም ማህበራቱ ያለባቸውን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር በመፍታት ውጤታማ ሥራ ለማከናወን    ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡                                                                                                   ሃ                                                       ሃ                                                          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም