ፍርድ ቤቱ በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተጠርጣሪዎች ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ ቀጠሮ ሰጠ

68
ነሀሴ 13/2011 ፍርድ ቤቱ በነ ብርጋዲየር ጀነራል ተፈራ ማሞ፣በእነ ኮማንደር ጌትነት ሽፈራውና በእነ አበበ መልኬ በቀረቡ ሶስት መዝገቦች በአቃቢ ህግና በጠበቆች የቀረበውን የይግባኝ ክርክር አጠናቆ ለነሐሴ 16/2011 ዓ.ም ውሳኔ ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ። በሰኔ 15/2011 ዓ.ም.በተፈፀመ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተጠርጥረው በሶስት መዝገቦች ስር በሚገኙ 62 ተጠርጣሪዎች ላይ የተጀመረው ምርመራ ሳይጠናቅቅ ፍርድ ቤቱ ክስ እንድንመሰረት መወሰኑ ተገቢ አይደለም ሲልም አቃቤ ህግ ለፍርድ ቤቱ ክርክሩን አቅርቧል። የጊዜ ቀጠሮ በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ አለመገደቡን ጠቅሶ የምርመራ ቡድኑም እስካሁን ከ110 በላይ የምስክሮችና ከ210 በላይ የተከሳሾችን ቃል መቀበሉን ለፍርድ ቤቱ ገልጿል። አሁንም ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ተሳታፊ የሆኑ አዳዲስ ተጠርጣሪዎች እየተያዙና በቁጥጥር ስር እየዋሉ በመሆኑ ለፍርድ ቤት በቀረበ ጉዳይ ላይ ህጉ ይግባኝ መጠየቅን አይከለግልም ሲልም አስረድቷል። ምርመራችንን አጣርተን ሳንጨርስ ክስ መመስረት ስለማንችል በቂ የምርመራ ጊዜ ሊሰጠን ይገባል ሲልም አቃቢ ህግ ጥያቄውን ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል። የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው የጊዜ ቀጠሮ ይግባኝ የሚቀርብበት እንዳልሆነ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ህጉ ላይ በግልፅ ተመላክቷል ብለዋል። የስር ፍርድ ቤቱ የሰጠው ውሳኔ ምክንያታዊ እንዳልሆነ በማሰብ አቃቤ ህግና የምርመራ ቡድኑ ያቀረበው ይግባኝ ትክክል ባለመሆኑ ፍርድ ቤቱ በአግባቡ ተገንዝቦ ይግባኙን ውድቅ እንዲያደርገውም ጠይቀዋል። የቴክኒክ ምርመራ የሚካሄደው በመንግስት ተቋማት በመሆኑ የምርመራ ቡድኑ ከምርመራው ጎን ለጎን ማየት ሲገባው የስር ፍርድ ቤቱ የጊዜ ቀጠሮውን ከዘጋው በኋላ የጊዜ ቀጠሮ ይሰጠኝ ብሎ ይግባኝ መጠየቁም ተገቢ አይደለም ሲሉ የተከሳሽ ጠበቆች ተከራክረዋል። የባህርዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ62 ተጠርጣሪዎች በቀረቡ ሶስት መዝገቦች በአቃቤ ህግና በተከሳሽ ጠበቆች የቀረቡ የይግባኝ ክርክሮችን ካዳመጠ በኋላ በመቅረፀ ድምፅ የተያዘው የተከራካሪዎች ቃል እስከ መጭው ሐሙስ ተገልብጦ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል። በክርክሩ ላይ ተመስርቶም ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ለመስጠትም ለነሓሴ 16/201 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም