የምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች አንድነታቸው እየተጠናከረ መጥቷል-አፈ-ጉባዔ ሐብታሙ - ኢዜአ አማርኛ
የምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች አንድነታቸው እየተጠናከረ መጥቷል-አፈ-ጉባዔ ሐብታሙ

አሶሳ ነሐሴ 13 ቀን 2011 በምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኙ ክልሎች አንድነታቸውን በማጠናከር ለአገር ልማት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እያደገ መምጣቱን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባዔ ገለጹ፡፡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፣ ኦሮሚያ ፣ አማራና ጋምቤላ ክልሎች የጋራ መድረክ ዛሬ በአሶሳ ተጀምሯል፡፡ ዋና አፈ-ጉባዔው አቶ ሐብታሙ ታዬ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት በምዕራብ የአገሪቱ ክፍል የሚገኙት ክልሎች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በልማትና በሠላም ሕዝቦቻቸውን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው፡፡ የክልሎቹ ግንኙነት ዘላቂ ልማት በማስፈን ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲረጋገጥ በሕገ-መንግሥቱ የተቀመጠውን አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እያፋጠነ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ በዚህ ረገድ የአማራና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝና ኦሮሚያን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና የጋራ የልማትና የሠላም እቅድ አተገባበር በአብነት አቅርበዋል። ይህም በተለይም የወጣቶችን ተስፋ እያለመለመ መሆኑን አቶ ሐብታሙ ተናግረዋል፡፡ በአንጻሩ ዓለም የደገፈውን ለውጥ ትርጉም መረዳት ያቃታቸውና ለማደናቀፍ የሚሯሯጡ አካላት እንዳሉም ገልጸዋል፡፡
ጽንፈኛ አመለካከት በመያዝ ለዘመናት በኖሩ ሕዝቦች ላይ ባደረሱት ጥፋት በሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውሰዋል፡፡ ክልሎቹ በድርጊቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሳተፉ ለፍርድ በማቅረብ የሕግ የበላይነት እንዲከበር ጥረት ማድረጋቸውንና በርካታዎቹ ለፍርድ መቅረባቸውን ዋና አፈ ጉባዔው አስታውሰዋል፡፡ ተፈናቃዮችን ወደ ቀደመው መኖሪያቸው ለመመለስ ክልሎቹ ያደረጉትን ጥረት መደረጉንና በዚህም የተገኘውን ውጤት በማጠናከር የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ልናጠናክር ይገባል ብለዋል፡፡ በመድረኩ የቤኒሻንጉል ጉሙዝና ኦሮሚያ ክልሎች በሠላምና በጸጥታ ረገድ ያከናወኗቸውን ተግባራት ወደ ዞኖች የሚያወርዱበት ስምምነት የሚያደርጉ ሲሆን፣ ጋምቤላና አማራ ክልሎች ደግሞ ተሞክሮ እንደሚቀስሙ ተገልጿል፡፡ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የግጭት አፈታትና የሠላም እሴቶች ግንባታ ኬዝ ማናጀር አቶ ሙስጠፋ ናስር በመድረኩ የምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ ፌደራሊዝምና የመንግሥታት ግንባታ የሚያተኩሩ ጥናታዊ ጽሁፎች በወለጋ ዩኒቨርሲቲ፣ በሕዝብ ተወካዮችና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች እንደሚቀርቡ አስታውቀዋል፡፡ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው መድረክ የአራቱ ክልሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡
