ፊፋ ለቀጣይ አራት ዓመታት የ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በጀት መደበ

51
አዲስ አበባ ሰኔ 6/2010  የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማህበር ፊፋ በቀጣይ አራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለሚያከናውናቸው ተግባራት የሚውል የ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በጀት መድቧል። ፊፋ ዛሬ በሩሲያ ርዕሰ መዲና ሞስኮ 68ኛ ጠቅላላ ጉባኤ አድርጓል። ጠቅላላ ጉባኤው ፊፋ እ.አ.አ ከ2019 እስከ 2022 ለሚያከናውናቸው ስራዎች ይውል ዘንድ የቀረበውን የ6 ነጥብ 56 ቢሊዮን ዶላር በጀት አጽድቋል። ከተመደበው በጀት 80 በመቶው ለእግር ኳስ እንቅስቃሴዎች የሚውል ሲሆን የተቀረው 20 በመቶ በጀት ፊፋ ከእግር ኳሱ ውጭ ለሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች ይውላል። በሌላ በኩል የፊፋ ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ  ግንቦት 28 ቀን 2011 ዓ.ም በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ በሚካሄደው የፊፋ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በድጋሚ ለመመረጥ እንደሚወዳደሩ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል። 'ፊፋ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በሙስና ምክንያት ያጣው ክብርና ዝና እንዲመለስ በማድረግ እንደ ተቋም የተሻለ ቁመና ላይ እንዲገኝ አድርጌዋለሁ' ብለዋል። ዛሬ በተካሄደው 68ኛው የፊፋ ጠቅላላ ጉባኤ እ.አ.አ በ2026 የሚካሄደውን የዓለም ዋንጫ ካናዳ ሜክሲኮና አሜሪካ በጥምረት እንዲያዘጋጁ ተወስኗል። 69ኛው የፊፋ ጠቅላላ ጉባኤ ግንቦት 28 ቀን 2011 ዓ.ም በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ ይካሄዳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም