መንግስት የህግ የበላይነትን በማስከበር በኦሮሞ ህዝብ ስም የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ሊያስቆም ይገባል---የገላና ወረዳ ነዋሪዎች

73
ነገሌ (ኢዜአ) ነሀሴ 12 ቀን 2011 መንግስት የህግ የበላይነትን በማስከበር በኦሮሞ ህዝብ ስም የሚፈጸሙ የግድያና የዘረፋ ወንጀሎች እንዲያስቆም የምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ ነዋሪዎች በሰላማዊ ሰልፍ ጠየቁ፡፡ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የተገኙ የወረዳው አመራሮች በበኩላቸው በዞኑ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የወረዳው ህዝብ የጥፋት ኃይሎችን በማጋለጥና ከጸጥታ አካላት ጋር ተባብሮ በመስራት ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል በገላና ወረዳ የወዶ ገርባ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ታምራት ባልቻ እንዳሉት በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ተባብሮ መስራት ያስፈልጋል። መንግስት የህግ የበላይነትን በማስከበር በኦሮሞ ህዝብ ስም እየተፈጸመ ያለውን ግድያና ዘረፋ እንዲያስቆም በሰላማዊ ሰልፍ ሲጠይቁ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑንም አመልክቷል። በጥፋት ኃይሎች ዛቻና ማስፈራሪያ የአዝመራ ስራቸውን እንደፈለጉ ለመስራትና ከቤት በሰላም ወጥቶ ለመመለስ ስጋት ውስጥ መውደቃቸውንም ጠቁመዋል፡፡ “የጥፋት ኃይሎች ህገወጥ እንቅስቃሴ ከዕለት ወደ እለት እየተባባሰ በመምጣቱ መንግስት ጠንከር ያላ ህጋዊ ርምጃ ካልወሰደ ለሕይወታችንም ሆነ ለንብረታችን ዋስትና የለንም” ብለዋል፡፡ የመንግስት ትዕግስት ለጥፋት ኃይሎች የፈለጉትን እንዲያደርጉ እድል ሲሰጥ ነዋሪው ህዝብ ተሸማቆ እንዲኖር እያደረገ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በእዚሁ ወረዳ የቶሬ ከተማ ነዋሪ አቶ ውዴሳ ገመዴ ናቸው፡፡ መንግስት የህግ የበላይነት እንዲከበር እየሰራ ቢሆንም በምዕራብ ጉጂ ዞን ቤት የሚቃጠልበት፣ ንብረት የሚዘረፍበትና ዜጎች የሚሳደዱበት ሁኔታ መኖሩን ገልጸዋል፡፡ “በዞኑ እየተፈጸመ ያለውን የህግ ጥሰት ለማስቆም የጥፋት ኃይሎችን በማጋለጥ የድርሻችንን እንወጣለን” ያሉት አቶ ውዴሳ፣ መንግስት ከህዝብ ጋር ተባብሮ በመስራት ሰላማቸውን እንዲያረጋግጥላቸው ጠይቀዋል። “በየጊዜው በዛቻና ማስፈራሪያ በስጋት ውስጥ እየኖርን ነው” ያሉት የእዚሁ ከተማ ነዋሪ አቶ ሰሊ ባነታ በበኩላቸው፣ መንግስት የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ የጥፋት ኃይሎችን አደብ ሊያስገዛ እንደሚገባ ነው የገለጹት ፡፡ “መንግስት የጥፋት ኃይሎችን ትጥቅ በማስፈታት ህግ ያስከብር እኛም ከመንግስት ጎን በመሆን አጥፊዎችን በማጋለጥ የድርሻችንን እንወጣለን” ሲሉም ተናግረዋል፡፡ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የተገኙት የምዕራብ ጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጃርሶ ዱጎ በበኩላቸው የህግ የበላይነትን ለማስከበር በመንግስት በኩል እየተሰራ ቢሆንም ያለህዝብ ተሳትፎ ውጤታማ መሆን እንደማይቻል ተናግረዋል። “የጥፋት ኃይሎች ከዛሬ ነገ ተመክረው ወደ ሰላማዊ ሕይወት ይመለሳሉ በሚል እንጂ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን መንግስት ይረዳል” ብለዋል። በአጥፊዎች ላይ መንግስት ከመምከር ባለፈ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን የጠቆሙት ዋና አስተዳዳሪው ሰሞኑን በገላና ወረዳ የህግ የበላይነትን የማስከበር ሥራ መስራቱን በማሳያነት ገልጸዋል። በእዚህም ከወረዳው ህዝብ ጋር በመተባበር በተደረገ አሰሳና የተኩስ ልውውጥ 3 የታጣቂ ቡድን አባላት ሲገደሉ 42 በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል፡፡ የተጀመረው የህግ የበላይነትን የማስከበር ሥራ በትዕግስትና በሆደ ሰፊነት ብቻ የማይቆምና ወደኋላ የማይመለስ በመሆኑ የወረዳውም ሆነ የዞኑ ህዝብ አስፈላጊውን ትብብርና ተሳትፎ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ ትናንት በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን ሰልፈኞችም ”በሽፍታ እየጠፋ ያለው የሰው ሕይወትና የንብረት ዘረፋ ይቁም! ፣ የህግ የበላይነት ይከበር! የጥፋት ኃይሎች የኦሮሞን ህዝብ አይወክሉም! “ የሚሉና ሌሎች መፈክሮች አሰምተዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም