የህጻናት የማስ ስፖርት በርካታ ህጻናትና ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት በአዲስ አበባ ተካሄደ

168
አዲስ አበባ ኢዜአ ነሀሴ 12 / 2011 'ደስተኛ ህጻናት ለአዲስ አበባ' በሚል መሪ ሃሳብ የህጻናት የማስ ስፖርት በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ተካሄደ። በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተካሄደው በዚህ  የማስ ስፖርት እንቅስቃሴ ዝናብና ብርዱ ሳይበግራቸው በርካታ ህጻናት በተገኙበት ተካሂዷል። የአዲስ አበባ ሴቶችና ህፃናት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ አልማዝ አብርሃ ''ነገ ላይ ጥሩ ትውልድ ለመፍጠር ዛሬ በህጻናት ላይ ሰፊ ስራን  መስራት የግድ ነው'' ብለዋል። ለዚህም የከተማዋ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ከመዲናዋ አስተዳደር ጋር በመሆን ሰፊ ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። ከእነዚህ መካከልም የህጻናት የምገባ ፕሮግራም ፣ ለተማሪዎች የደብተርና እስኪርቢቶ አቅርቦት፡ ዩኒፎርም ማልበስና ሌሎች ስራዎች በእቅድ ተይዘው እየተሰሩ ነው ብለዋል። የዛሬው የማስ ስፖርትም ጤናማና ደስተኛ ህጻናት እንዲኖሩን ለማድረግ ትልቅ ድርሻ አለው ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ ህጻናትን እርስ በእርሳቸው ጥሩ ግንኙነት እንዲኖራቸውና ቤተሰብም ከልጆቹ ጋር ሰፊ ጊዜ ሰጥቶ በጋራ ለመዋል እድል ይፈጥርላቸዋል ብለዋል። ይህ የህፃናት የማስ ስፖርት በየሳምንቱ በየካባቢያቸው በተመረጡ ቦታዎች የሚቀጥል ሲሆን በየስድስት ወሩ ደግሞ መስቀል አደባባይ ላይ የሚከናወን ይሆናልም ተብሏል። የፌደራል  የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ወይዘሮ ያለም ጸጋዬ በበኩላቸው  በቀጣይ በሌሎችም ክልሎች ይህን ተሞክሮ ለማስፋት በጋር እንደሚሰሩ ገልጸው፤ ይህ ዝግጅት እንዲሰካ የበኩላቸውን ሚና ለተወጡ አካላትም ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል። በዛሬው የህጻናት የማስ ስፖርት እንቅስቃሴ ላይ  አሳዳጊ የሌላቸው ህጻናትን በጉድፈቻ ለማሳድግ ሁለት እናቶች ሁለት ልጆችን ወስደዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም