በከተማዋ የዲጂታል መታወቂያ አሰራር ከመጪው መስከረም ጀምሮ በሁሉም ወረዳዎች ተግባራዊ ይሆናል

54
አዲስ አበባ ኢዜአ ነሃሴ 12/2011በአዲስ አበባ ከተማ የዲጂታል መታወቂያ አሰራር በመጪው መስከረም መጨረሻ በሁሉም ወረዳዎች ተግባራዊ እንደሚሆን ተገለጸ። የአዲስ አበባ የወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ዋና ዳሬክተር ወይዘሮ ብሩክነሽ አርጋው በተለይም ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማዋ የዲጂታል መታወቂያ ተግባራዊ ለማድረግ የናሙና ሙከራ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አሁንም እየተደረገ ይገኛል። ይህንን መሰረት በማድረግም በሁሉም ክፍለ ከተሞች አሰራሩን ለመተግበር አስቻይ ሁኔታዎችና ችግሮች መለየታቸውንም ጠቁመዋል። እንደ ዳሬክተሯ ገለጻ በቀሩት 9 ክፍለ ከተሞች ለመተግበር የግብዓትና የባለሙያዎች የመፈጸም አቅምንም ለማየት ተሞክሯል። በተደረገው ማጣራትም በሁሉም ክፍለ ከተሞች 11 ወረዳዎች በግብዓት፣ በአደረጃጀትና በመሰረተ ልማት ችግር አሁን ባሉበት ደረጃ የዲጅታል መታወቂያን ስራ መጀመር የማይችሉ መሆናቸው ተለይተዋል። እነዚህ ወረዳዎች በከተማዋ ማስፋፊያ አካባቢዎች የሚገኙ መሆናቸውን ጠቁመው ችግሮችን በመፍታት ወደ ስራ አንዲገቡ ሁሉም በየደረጃው የሚገኝ ሃላፊ በትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል። ሌሎች በ10 ክፍለ ከተሞች የሚገኙ 65 ወረዳዎች ያሉባቸውን ችግሮች በማሻሻል ከማኑዋል መታወቂያ ጎን ለጎን የዲጂታል መታወቂያ መስጠት የሚያስችላቸው ሁኔታ ላይ በመሆናቸው ስራው መጀመሩን ገልጸዋል። በመሰረተ ልማትና ሌሎች ችግሮች ዲጂታል መታወቂያውን መስጠት የማይችሉበት ሁኔታ ሲፈጠርም በቀድሞው የማኑዋል መታወቂያ እንዲያወጡ በማድረግ ችግሮችን የማስተካከል ተግባር እንደሚከናወንም ነው የጨመሩት። የሲስተም መቆራረጥ ትልቅ ችግር እንደሆነባቸው የገለጹት ዳሬክተሯ፤ ከቴሌና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። እንደ ዳሬክተሯ ገለጻ ከሆነ አሁን ስራውን ማከናወን የማይችሉ ወረዳዎችን ጨምሮ የመሰረተ ልማትና ሌሎች ችግሮችን በማስተካከል በመጪው መስከረም መጨረሻ ላይ ሁሉም ወረዳዎች የዲጂታል መታወቂያ መስጠት ይጀምራሉ። በከተማዋ እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ ትክክለኛ ባልሆኑ መታወቂያዎች የሚፈጸም ህገ ወጥ ድርጊት ሰፊና መቆጣጠር ያልተቻለ መሆኑ ይነገራል። የዲጂታል መታወቂያ በትክክል ተግባራዊ ከተደረገ የዚህን መሰል ችግሮች ለመፍታት የሚችል ሲሆን እንድ መታወቂያ በአንድ ሰው ስም አንድ ጊዜ ከተመዘገበ ማንም ሰው ደግሞ መውሰድ እንደማይችል ተደርጎ ይዘጋጃል። መታወቂያው ህገ ወጥ ድርጊትን ለመከላከል የሚያግዝ ሲሆን ግለሰቦች እንዲሁም የገንዘብና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ተጠቃሚ ይሆናሉ። ቀደም ሲል የነበረው የማኑዋል መታወቂያ የግለሰቡን ቤት ቁጥር፣ ወረዳና ሌሎች መረጃዎችን የያዘ ሲሆን የዲጂታል መታወቂያው ግን አንድ ወረዳን ብቻ ሳይሆን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪነትን፣ አሻራን፣ የአይን ቀለምን፣ የደም አይነትንና ሌሎች መገለጫዎችን በውስጡ ማካተቱ ከወትሮው ይለየዋል ተብሏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም