ወጣቶች የስደትን መራራነት ተረድተው ከስደት መታቀብ አለባቸው - በሱዳን ተመላሽ ስደተኞች

56
ነሐሴ 12/2011 ወጣቶች ከእኛ ስቃይ የስደትን መራራነት ተረድተው ከስደት መታቀብ አለባቸው ሲሉ በሱዳን ውሰጥ በእስር ቆይተው የተመሰሉ ስደተኞች ተናገሩ። በተለያዩ እስር ቤቶች ቆይተው በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተጠልለው የነበሩ ከ100 በላይ ስደተኞች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ ገብተዋል። ለእንጀራ ፍላጋ ስደትን የናፈቁ አብዛኞቹ ወንዶች ወደ አውሮፓ፣ ሴቶቹ ደግሞ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ለመሻገር የደላላዎችን አመራጭ ይጠቀማሉ። ደላሎቹ በተለይም ህገወጦቹ ደግሞ ሰዎችን ከአገር ለማስወጣትና ለማዘዋወር ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች መካከል አንዱ የመተማ-ሱዳን-ሊብያ መስመር ተጠቃሽ ነው። ወጣት ቴዎድሮስ ሰዋገኝም ከአራት ዓመታት በፊት ሜደትራኒያን ባህር አቋርጦ አውሮፓ ተሻግሮ እንጀራውን ለማብሰል ነበር የመተማን መስመር በመጠቀም በደላሎች ጎዳና ሊቢያ የገባው። ከ80 ሺህ ብር በላይ ለደላሎች ከፍሎ ሊብያ የደረሰው ቴዎድሮስ ግን 'ጽድቁ ቀርቶ...' እንዲሉ አውሮፓ ለመድረስ ቀርቶ በሊብያ ጠረፍ ታስሮ፣ ሌሊት ሌሊት በነጻ የህንጻ ስራዎችን እየሰራ ህይወቱን መግፋት ቀጠለ። ተጨማሪ ገንዘብ አምጡ በሚልና በሌሎች የደላላ ትዕዛዛት ሳቢያ ሌሎች 13 ጓደኞቹ ሲገደሉ ብቻውን መቅረቱንም በቁጭት ያነሳል። በአምስት ጥይት እጁን ተመቶ መትረፉን የሚተርከው ቴዎደሮስ፤ በፈጣሪ ቸርነት በህይወት ለአገሩ በመብቃቱ ደስታውን ለመግለጽ እግሩ ገና መሬት ሳይነካ በአውሮፕላኑ ደረጃዎች ላይ ሆኖ ነበር ገጹን ትምህርተ መስቀል ማማተብ የጀመረው። ከ20 ዓመታት በፊት ለቀን ስራ ብለው ከአገር መውጣታቸውን የሚገልጹት ደግሞ አቶ ግርማ ይስማው ናቸው። በሱዳን ቆይታቸው ክፉ ደጉን ህይወት እየመሩ ቆይተው ከወራት በፊት 'በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ...' እንዲሉ የመኪና አደጋ ደርሶባቸው በኢትዮጵያ ኤምባሲና ማህበረሰብ ድጋፍ ህክምና ተደርጎላቸው ህይወታቸው መትረፉን ይናገራሉ። በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ የሚደርሰውን መከራና የክብር መዋረድ የተመለከተው ቴዎድሮስ፤ ዛሬ ላይ 'ኢትዮጵያን ያዋረድናት እኛ ነን፤ አንድ ዳቦ ተካፍለን ብንበላ ይሻለናል' ሲልም ይመክራል። 'ስደት መራራ ነው' የሚሉት አቶ ግርማም በሰው አገር ቆይታቸው የተመለከቱትን አስከፊ የህይወት ገጾች በመግለጽ፤ ሌሎች ከእኛ ሊማሩ ይገባል ነው ያሉት። የስደት አስከፊ ገፈት ቀማሾች ወንዶች ብቻ አይደሉም። በህገ ወጥ ደላላ አማካኝነት ወደ መካከለኛው ምስራቅ በየጊዜው የሚተሙ ሴት ወጣቶችም ቆይታቸው መራራ ነው። ሳግ እየተናነቃት "ስደት በተለይ ለሴት ልጅ አይመችም" የምትለው ሰሚራ መሃመድ፤ "ስደት በእኛ ይቅር፣ አገራችን ላይ ቡና አፍልተን መኖር ይሻለናል" ትላለች። ሰሚራና አብዛኞቹ ጓደኞቿ ከአራት ወራት በፊት በመተማ በኩል ወጥተው ወደ ቤይሩት፣ ዱባይና ሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ለመሄድ በደላሎች እንደ ዕቃ መለዋወጣቸው፣ በመጥፎ የአየር ሁኔታ መሰቃየታቸው፣ ገንዘብ መከስከሳቸው ከደረሰባቸው ስቃዮች ናቸው። በደላሎች እጅ ህገ ወጥ ቪዛ ሲጠባበቁ የቆዩት እነ ሰሚራ፤ የአገሪቷ ፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ሱዳን ውስጥ በእስር ህይወት መዳረጋቸውንም ይገልጻሉ። ከእስር ቤት ከወጡ በኋላም በካርቱም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተጠልለው ቆይተው ትናንት ከጠቅላይ ሚኒሰትሩ ጋር ወደ አገራቸው በመመለሳቸው ምስጋና አቅርበዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም