የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ፕሮጀክቶችን ጎበኙ

61
ሐረር ነሐሴ 11 / 2011 የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ የሚመራ ቡድን በክልሉ እየተካሄዱ ያሉትን ፕሮጀክቶች ዛሬ ጎበኘ፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ የተጓተቱ ፕሮጀክቶች እንዲፋጠኑ አሳስበዋል። ከተጎበኙት የልማት ፕሮጀክቶች መካከል ግንባታ 17 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ ግንባታቸው ተጀምሮ የተጓተተው ከኤረር በር እስከ ኤረር ወልድያ ያለው የዘጠኝ ኪሎሜትር የገጠርመንገድ ጥገናና  የኤረር ድልድይ ግንባታ ይገኙበታል። እንዲሁም ለገጠሩ ኅብረተሰብ የሙያ ስልጠና መስጠት ያስችላል የተባለውና በ2 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ግንባታው በመጠናቀቅ የሚገኘው የስልጠና ማዕከልም ተጎብኝቷል፡፡ በሐረር ከተማ በ160 ሚሊየን ብር ወጪ ግንባታቸው  በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙት የራስ መኮንን ትምህርት ቤትና የጠቅላይ ፍርድ ቤት የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች እንዲሁም የአፈ ጉባዔና  የፕሬዚዳንት  ጽህፈት ቤት ሕንጻ  ፕሮጀክቶችም በጉብኝቱ ተካተዋል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት የአንዳንድ ፕሮጀክቶች የተሻለ መሆኑን ገልጸዋል። ሆኖም የተጓተቱ ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ  በዋናነት የዝግጅት  ምዕራፍ ሥራዎች በተገቢው መልኩ አለመከናወናቸውና   የማስፈፀም አቅም ውስንነት  እንዲሻሻሉ አሳስበዋል፡፡ በተለይም የኮንትራክተሮች አቅም ማነስ ለፕሮጀክቶቹ መጓተት ምክንያት መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡ የመስክ ምልከታውም ያሉ ጠንካራ ጎኖችንና ክፍተቶችን በመለየት ለዝግጅት ምዕራፉ በግብዓትነት መጠቀም እንደሚገባ አቶ ኦርዲን አሳስበዋል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት ችግሮቹን በሚፈታ መልኩ ዝግጅት በቨማድረግ  ከሕዝብ ፍላጎት አንፃር ቅድሚያ የሚሰጣቸው ፕሮጀክቶች ተለይተው እንደሚሰሩ አስታውቀዋል ፡፡ በተለይም ኅብረተሰቡን ወደ ልማት የሚያስገባና የገጠሩን ማህበረሰብን የሚጠቅሙ የልማት ሥራዎች  ትኩረት ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡ የክልሉ መንገዶች ባለስልጣን መሐንዲስ አቶ ደጀኔ አበራ በተለይ ፕሮጀክቶች የተጓተቱት በአገሪቱ በነበረው ወቅታዊ ጉዳዮችና የግንባታ ጥሬ እቃ ዋጋ በመናሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ስለሆነም ከኤረር በር ኤረር ወልዲያ ያለው የገጠር ጥርጊያ  መንገድ በሁለት ወራት ጊዜ ሥራ እንደሚጀምርና  የኤረር ድልድይ ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል፡፡ በጉብኝቱም ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ የካቢኔ አባላት፣ የሴክተር መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም