በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ከ10 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል

73

ነሀሴ 11/2011በምርት ዘመኑ ከ10 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ መሆኑን በኦሮሚያ ክልል የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ገለፀ።

የታሰበውን ምርት ለማግኘት 330 ሺህ ሄክታር መሬት መልማቱን የገለጸው የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ነው።

ከመሬት ዝግጅት ባሻገር የምርጥ ዘርና ማዳበሪያ አቅርቦት ሥራ መከናወኑን የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ብርሀኑ ለሜሳ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ምክትል ኃላፊው ባለፈው ዓመት የምርት ዘመን 330 ሺህ ሄክታር የሚሆን መሬት ታርሶ ከ8 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የተለያዩ ሰብሎች ምርት መገኘቱን አውስተዋል።

ዘንድሮ የሚመረተው ምርት በጥራትና በብዛት እንዲጨምር ከማሳ ዝግጅት እስከ ምርት ስብሰባ ድረስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በዞኑ የሚመረቱትን ጤፍ፣ ስንዴና በቆሎ፤ የቅባት እህሎች፤ ሽንብራ ባቄላና አተር በጥራት ለማምረት ዝግጅት ተደርጎ ወደ ሥራ መገባቱን አክለዋል።

የዞኑ አርሶ አደሮች የግብርና ሜካናይዜሽን የመጠቀም ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የገለፁት አቶ ብርሃኑ ፍላጎትና አቅርቦቱ ባለመመጣጠኑ በወረፋ እየተጠቀሙ መሆኑንም ተናግረዋል።

ችግሩ እንዲፈታ መንግስት ተጨማሪ ትራክተሮችና ሌሎች የእርሻ መሳሪያዎችን እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

በዞኑ የወሊሶ ወረዳ ጽህፈት ቤት የግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቱፋ ኤጀታ በበኩላቸው የወረዳውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ለአርሶ አደሮች እየተደረገ ስላለው ድጋፍ ገልፀዋል።

በምርትና ምርታማነት ዙሪያ ስልጠና ከመስጠት እስከ ማሳ ዝግጅት እንዲሁም በመስመር መዝራትና ሌሎች የግብዓት አቅርቦት ድጋፍ እንደሚደረግ ነው የተናገሩት።

የወሊሶ ወረዳው አርሶ አደር ሸለመ ቤካ በግብርና ባለሙያዎች በሚደረግላቸው ድጋፍ ምርትና ምርታማነታቸው እያደገ ስለመምጣቱ ለኢዜአ ተናግረዋል።

በብተና በሚዘሩበት ጊዜ የሚያገኙት ምርት አጥጋቢ እንዳልነበር ገልፀው በመስመር መዝራት ከጀመሩ በኋላ በሄክታር የሚያገኙት ምርት መጨመሩን ለአብነት አንስተዋል።