በሆሳእና ከተማ 138 የባለ ሁለት እግር ሞተር ሳይክሎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

136
ሆሳዕና ነሐሴ 11/2011 በበደቡብ ክልል ሆሳእና ከተማ 138 ሞተር ብስክሌቶች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ኮማንድ ፖስቱ ዛሬ ገለጸ፡፡ የከተማው ሰላምና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የኮማንድ ፖስት አባል አቶ ዳዊት ኪበሞ ለኢዜአ እንደገለጹት ሞተር ቢስክሌቶቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ለኅብረተሰቡ ደህንነት ስጋት በመሆናቸው ነው፡፡ ሠሌዳ ቁጥር ሳይኖራቸው ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው አገልግሎት እንዳይሰጡ መታገዳቸውን አስረድተዋል። ኮማንድ ፖስቱ የአካባቢዉን ኅብረተሰብ ደህንነት ለስጋት የሚጥሉ ጉዳዮችን በመለየት እርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ በከተማው ሠሌዳ ቁጥር ሳይኖራቸው የሚንቀሳቀሱ ሞተር ቢስክሌቶች መበራከት ኅብረተሰቡን ከዝርፊያ ባሻገር፤ለሞት እየዳረገው መሆኑን አቶ ዳዊት አስታውቀዋል፡፡ የሐድያ ዞን ብሎም አካባቢዉ ከወቅቱ የደቡብ ክልል ነባራዊ ሁኔታ አንጻር የኅብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በኮማንድ ፖስት እንዲመራ መደረጉን አስታውሰዋል። ከከተማው ነዋሪዎች የቤቴል ቀበሌ ነዋሪው አቶ ዮሐንስ ሱላሞ በሰጡት አስተያየት በሞተር ቢስክሌቶቹ ላይ የተወሰደው እርምጃ የዜጎችን ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ያስችላል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡ የሞተር ቢስክሌቶቹ አሽከርካሪዎች የትራፊክ ሕግን የማያከብሩ ከመሆናቸውበላይ ዜጎቸን ለሞትና ለአካለ ስንኩልነት ዳርገዋል ብለዋል፡፡ ቁጥጥሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡ ''ያለ ታርጋ በማሽከርከር የተለያዩ አደጋዎች በማድረስ እንዲሁም የሴቶችን ቦርሳ በመቀማት ይሰወሩ እንደነበርና በተለይም ሴቶች ለደህንታቸው ስጋት አሳድሮባቸዋል'' በማለት አስተያየቷን የሰጠችው የሜል አምባ ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሪት ምህረት ከበደ ናት፡፡ ለኅብረተሰቡ ደህንነት ሲባል ክትትልና ቁጥጥሩ መጠናከር እንዲከበር ጠይቃለች።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም