የፈረንሳዩ ማልተሪዬስ ሶፍሌት ኩባንያ በኢትዮጵያ የብቅል ማምረቻ ኢንዱስትሪ ሊገነባ ነው

102
አዲስ አበባ ሰኔ 6/2010 የፈረንሳዩ ማልተሪዬስ ሶፍሌት ኩባንያ በ50 ሚሊዬን ዶላር በኢትዮጵያ የብቅል ማምረቻ ኢንዱስትሪ ሊገነባ መሆኑን አስታወቀ። በግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ለገበያ በማቅረብ የሚታወቀው ይህ ኩባንያ በአዲስ አበባ ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ብቅል ለማምረት የሚያስፈልገውን መሬት በሊዝ ለመውሰድ የሚያስችለውን ስምምነት ዛሬ ተፈራርሟል። ለ70 ዓመት የሚቆየውን የሊዝ ስምምነት የፈረሙት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንና  የማልተሪዬስ ሶፍሌት ኩባንያ ናቸው። የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ክርስቶፍ ፓሴላንዴ በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ ሰፊ የገብስ አብቃይ ከሆኑ የአፍሪካ አገሮች መካከል አንዷ መሆኗን ጠቅሰው ፋብሪካው ስራ ሲጀምር በዓመት እስከ 60 ሺህ ቶን ብቅል ማምረት ይቻላል ብለዋል። በ50 ሚሊዬን ዶላር የሚከናወነው የብቅል ማምረቻ ፋብሪካው ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከውጭ ለምታስገባው ብቅል የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ በግማሽ ከመቀነሱ በተጨማሪ ለ20 ሺህ ገብስ አምራች አርሶ አደሮችም የገበያ ትስስር ይፈጥራልም ብለዋል። ፋብሪካው በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የማምረት ሥራ እንደሚጀምር የሚጠበቅ ሲሆን ለ50 ሰራተኞች የስራ እድል እንደሚፈጥር የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ገልፀዋል። ኢትዮጵያ ትልቅ ገበያ ያላት፣ ትላልቅ ቢራ አምራች ድርጅቶች የሚገኙባትና ለሥራ ተስማሚ ሁኔታዎች የሚታዩባት ሀገር በመሆኗ ከአፍሪካ ተመራጭ ማድረጋቸውንም ጨምረው ጠቅሰዋል። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሌሊሴ ነሜ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በሀገሪቱ ለሚገኙ ቢራ ፋብሪካዎች የሚያስፈልገውን 70 በመቶ ብቅል የምታስመጣው ከውጭ መሆኑን አስታውቀዋል። የኩባንያው ኢትዮጵያ ውስጥ መከፈት ይህንን የውጭ ምንዛሬ ወጪ ከመቀነስ ባለፈ ለገብስ አምራች አርሶ አደሮች ጠንካራ የገበያ ትስስር በመፍጠር ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል ብለዋል። ወይዘሮ ሌሊሴ ኩባንያው ለወጣቶችና ሌሎች ሥራ ፈላጊዎች ጊዜያዊና ቋሚ የሥራ እድል በመፍጠር ለአገሪቱ ምጣኔ ኃብታዊ እድገት የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር በላቸው መኩሪያ ኩባንያው በአገሪቱ ያለውን ከፍተኛ የብቅል ፍላጎት ከማሟላት  በተጨማሪ  የገብሰ አምራች አርሶ አደሩሮች ስራን ያሻሽላልም ብለዋል። ለግብርናው ዘርፍ መዘመንና ለአገሪቱ ምጣኔ ኃብታዊ እድገት ከድርጅቱና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም