የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ማዕከል በሁመራ ሰሊጥ የሚያገበያይበት ማዕከል ከፈተ

86

ሑመራ ነሐሴ 11 / 2011 በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ማዕከል የሁመራ ቅርጫፍ የሰሊጥ ምርትን በዘመናዊ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት የሚያገበያይበት ማዕከል ትናንት ከፈተ።

በከተማው የተከፈተው ማዕከል ነጋዴዎችና የሰሊጥ አምራች አርሶ አደሮችን ወደ አዲስ አበባ መሄድ ሳያስፈልጋቸው በቀጥታ ለመገበያየት እንደሚያስችላቸው ተገልጿል።

ለማዕከሉ ዘመናዊ የኤሌከትሪኖክስ ማሽኖች የየተከሉለት ሲሆን፣የንግዱ ማህበረሰብና አርሶ አደሮች በቀጥታ ምርታቸውን በወቅቱ የዓለም ገበያና ተመጣጣኝ ዋጋ ለመሸጥ የሚያስችላቸው ነው ተብሏል።

በሁመራ የግብይት ማዕከሉ ዋና አስተባባሪው አቶ አታክልቲ አማረ ለኢዜአ እንደገለጹት የማዕከሉ በከተማው መከፈት ቀደም ሲል በሰሊጥ አምራችና አቅራቢነጋዴዎች ላይ ሲደርስባቸው የቆየውን ያላስፈላጊ ወጪና መጉላላት ያስቀርላቸዋል።

እንዲሁም ከአነስተኛ ነጋዴ እስከ አርሶ አደር ድረስ ምርቱን በፈለገው ዋጋ መሸጥ የሚያስችለው ነው ብለዋል።

እንደ አስተባባሪው ገለፃ ከሆነ፣ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ግብይቱ የአርሶ አደሩን አሳታፊነት በማሳደግ በኩልም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።

በሰሊጥ ንግድ ለ50 ዓመታት ያህል የተሰማሩት አቶ አዘዘው ቸኮል እንዳሉትም፣ቀደም ሲል በሰሊጥ ምርት ግብይት ላይ የአሰራር ግልጽነት የጎደለው ነበር።

በአሰራሩ ግልጽነት ጉድለት ምክንያትም አርሶ አደሩ ለፍቶ ያመረተውን ምርት በጥቂት ነጋዴዎች ተመጣጣኝ ባልሆነ ዋጋ በመሸጥ ሲበዘበዝ ቆይቷል ብለዋል።

መንግሥት ችግሩን በመገንዘብ በከተማው በከፈተው ዘመናዊ የግብይት ማዕከል አርሶ አደሩና አነስተኛ ነጋዴዎች ተጠቃሚ አንደሚያደርጋቸው ተስፋቸውን ገልጸዋል።

አሰራሩ በተለይ የከተማው ወጣቶችን ተጠቃሚነታቸው እንደሚያረጋግጥላቸው የተናገረው ደግሞ በሁመራ ከተማ የ01 ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ጋንቹ ይርጋ ነው።