ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨሲቲ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

75
ሶዶ ሚያዝያ 27/2010 ለወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትነት ሲወዳደሩ ከነበሩት እጩዎች መካከል ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ በአሸናፊነት መመረጣቸውን ዩኒቨርሲቲው አስታወቀ። የዩኒቨርሲቲው ኮሙኒኬሽንና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ለኢዜአ በላከው መረጃ እንዳመለከተው ከጥር 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ዩኒቨርሲቲውን በፕሬዝዳንትነት ሊመሩ የሚችሉ ምሁራንን ሲያወዳድር ቆይቷል። ውድድሩ በመስፈርትነት ያስቀመጣቸውን የትምህርት ደረጃ ፣የአካዳሚክ ማዕረግ ፣ የስራ ውጤት እንዲሁም የስትራቴጂክ እቅድ አቀራረብን በማካተት ከጥር 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ሲካሔድ ቆይቷል። የመጨረሻ ዙር ውድድር ዕጩ ሆነው ከቀረቡ ተወዳዳሪዎች መካከልም ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ሆነው እንዲቀጥሉ በትምህርት ሚኒስቴር ተመርጠዋል። በዩኒቨርሲቲው ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ በአካዳሚክ ትምህርት ክፍል በመምህርነትና በተመራማሪነት ያገለገሉ ሲሆን በተለያዩ የስራ ክፍሎች በከፍተኛ የሃላፊነት ቦታ መስራታቸውም ተመልክቷል። በአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንትነት እና በተጠባባቂ ፕሬዝዳንትነት ዩኒቨርሲቲውን ከማገልገላቸውም ባለፈ ለትምህርት ጥራትና መሻሻል፣ ለጥናትና ምርምር መጎልበት ወሳኝ የሆኑ ተግባራትን ማከናወናቸውንም መግለጫው ያሳያል። የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስተር በአዋጅ ቁጥር 650/2001 ዓ.ም በተደነገገው መሰረት የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶችን በማወዳደር የሚመድብ መሆኑ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም