የሲዳማ አባቶች ያቆዩትን የአብሮነት እሴት ጠብቆ ማቆየትና ማስቀጠል ይገባል...አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ

85
ሀዋሳ ኢዜአ ነሀሴ 10 / 2011-የሲዳማ አባቶች ያቆዩትን የአብሮነት እሴት ጠብቆ ማቆየትና ማስቀጠል እንደሚገባ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ ገለፁ ፡፡ የሲዳማ ብሔር ቋንቋና ባህል ሲምፖዚየም በሃዋሳ ከተማ ተካሂዷል፡፡ በሲምፖዚየሙ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ሚሊዮን እንዳሉት የራስን ቋንቋና ባህል ለማሳደግ አስቸጋሪ የነበረበት የአገዛዝ ዘመን ካለፈ በኋላ የሲዳማን ባህልና ቋንቋ ለማሳደግ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀዋል ፡፡ ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ሥራዎች የብሔሩን ቋንቋ የሥራና የትምህርት ቋንቋ ከማድረግ ባለፈ ባህሉንም በተገቢው መንገድ ማስተዋወቅ መቻሉን አስታውሰዋል ፡፡ የሲዳማ አባቶች ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር አብሮ የመኖርን እሴት ጠብቀው አሁን ላለው ትውልድ ማስተላለፋቸውን የጠቀሱት አቶ ሚሊዮን ይህንን መልካም እሴት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ነው ያመለከቱት ፡፡ "ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር የሚኖሩ ህዝቦች ከድህነትና ኋላ ቀርነት ተላቀው ወደፊት ለመራመድ ሰፊ እድል እንዳላቸው ጥናቶች ያመለክታሉ" ያሉት አቶ ሚሊዮን፣ በአካባቢ ካሉ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ተስማምቶ አብሮ በመኖር መለወጥ እንደሚቻል አመልክተዋል ፡፡ "የባህልና የሃይማኖት አባቶችንና ሽማግሌዎችን መስማት ያስፈልጋልም" ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የሲዳማ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጃጎ አገኘሁ በበኩላቸው ሲምፖዚየሙ ላለፉት 25 ዓመታት ሲካሄድ መቆየቱን አስታውሰዋል። በተካሄዱ ሲምፖዚየሞች ላይ የሲዳማን ባህልና ቋንቋ መሰረት ያደረጉ ጥናታዊ ፅሁፎችን ያቀረቡ ምሁራን የሚሰጧቸው ሀሳቦችንና ተሳታፊዎች ያነሷቸው ገንቢ አስተያየቶችን መነሻ በማድረግ በአስፈፃሚ አካላት በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል ፡፡ የብሔሩ ቋንቋ የሥራ ቋንቋ ከመሆኑ ባሻገር ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ትምህርትና ምርምር የሚካሄድበት ቋንቋ እንዲሆን መደረጉንም አስታውሰዋል። በተጨማሪም የብሔሩ ዘመን መለወጫ “ ፊቼ ጫምበላላ ” በዓል በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ ከተከናወኑ ተግባራት ውስጥ ተጠቃሽ መሆናቸውን ነው ያስረዱት ፡፡ "በሲዳማ ብሔር ቋንቋ “ ሲዳሙ አፎ ” የተለያዩ ሥነ ፅሑፎችና መዝገበ ቃላቶች መዘጋጀታቸውም የዚሁ ሥራ ውጤት ነው" ብለዋል ፡፡ አቶ ጃጎ እንዳሉት ቋንቋውን ይበልጥ ለማበልፀግና በአጠቃቀም ዙሪያ የሚታዩ ክፍተቶችን ከወዲሁ ለማረምም ከትምህርት ቤቶች ፣ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ቁርኝት ተፈጥሮ እየተሰራ ነው። ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በፍቅር የመኖር የአብሮነት ባህል የሲዳማ ህዝብ ከጥንት ጀምሮ ጠብቆ ያቆየው እንደሆነ የተናገሩት አቶ ጃጎ፣ በወቅታዊ የፖለቲካዊ ሁኔታዎችና ከግለሰቦች የግል ፍላጎት የተነሳ የሚፈጸሙ አንዳንድ ያልተገቡ ተግባራት የብሄሩን ባህል እንደማይገልጹ አስረድተዋል ፡፡ የተለያዩ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት በአባቶችና በአሁኑ ትውልድ መካከል ያለውን የባህል ክፍተት ለመሙላትና የብሔሩን እሴቶች ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል ፡፡ የሀገረሰላም አካባቢን ወክለው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነት እያገለገሉ ያሉትና በሲምፖዚየሙ ላይ የተሳተፉት አቶ ቡንቱቃ ዋሬ ላለፉት ዓመታት የሲምፖዚየሙ መካሄዱ በባህልና ቋንቋ እድገት ላይ ብዙ ጠቀሜታ እንዳስገኘ ገልፀዋል ፡፡ በአሁኑ ወቅትም በብሔሩ ቋንቋ ላይ በርካታ ጥናትና ምርምሮችን የሚያካሂዱ ምሁራንን ማፍራት መቻሉን አመልክተዋል፡፡ የሲዳማ ህዝብ አግላይነትን የማያውቅ እንግዳ ተቀባይ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ቡንቱቃ "በቅርቡ በዞኑ ተከስቶ የነበረው ያልተገባ ተግባር የህዝቡን ባህልና እሴት የሚገልጽ አይደለም" ብለዋል ፡፡ እንደዚህ አይነት ተግባር ዳግም እንዳይፈጠር ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበትና ወጣቱም ከተመሳሳይ ድርጊት ራሱን እንዲጠብቅ አስገንዝበዋል ፡፡ ከመልጋ ወረዳ የመጣው ወጣት ቢኒያም ቡጡላ በበኩሉ ለሲምፖዚየሙ ከተዘጋጀው የባህል አውደ ርዕይ በርካታ የማያውቃቸውን ባህላዊ ክዋኔዎችና ቁሳዊ ነገሮችን ለማወቅ መቻሉን ተናግሯል ፡፡ በቀጣይ በሚኖርበት አካባቢ ሌሎችን በማክበር አብሮ የመኖር እሴቶችን ጠብቆ ለማቆየት እንደሚጥር ተናግሯል ፡፡ ወጣቶችም በወቅታዊ ነገሮች ተነሳስተው አብሮ የመኖር አኩሪ ባህልን ከማበላሸት መቆጠብ ፣ አባቶችንና መሪዎችን መስማት እንዲሁም እርስ በእርስ መደማመጥ እንዳለባቸውም መክሯል ፡፡ በሲምፖዚየሙ የሲዳማንብሔርቋንቋናባህልየተመለከቱጥናታዊጽሁፎችበምሁራንየቀረቡሲሆንየብሔሩንባህላዊመስተጋብሮችየሚገልፁባህላዊቁሳቁሶች፣አልባሳትናምግቦችለዕይታቀርበዋል፡፡ በሲዳማ ዞን ከሚገኙ ወረዳዎች የመጡ ተወካዮች ፣ የባህል አባቶችና ሽማግሌዎች፣ ምሁራን እንዲሁም የዞን ፣ የደቡብ ክልልና የፌዴራል አካላት የሲምፖዚየሙ ተሳታፊዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም