በአዲስ አበባ እሁድ የሚካሄደው 4ተኛው አገር አቀፍ የጽዳት ዘመቻ ቅድመ ዝግጅቱ ተጠናቋል

97

አዲስ አበባ ኢዜአ ነሀሴ 10/2011 በመጪው እሁድ የሚካሄደው 4ተኛው አገር አቀፍ የጽዳት ዘመቻ በአዲስ አበባ በ10ሩም ክፍለ ከተሞች አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ።

‹‹እኔ አካባቢዬን አፀዳለሁ እናንተስ?›› በሚል መሪ ቃል ባለፈው ዓመት የተጀመረው አዲስ አበባን የማፅዳት ዘመቻ በየወሩ የመጨረሻ ቅዳሜ እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል።

የከተማዋ የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ እሸቱ ለማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በመጪው እሁድ ለሚካሄደው 4ተኛው አገር አቀፍ የጽዳት ዘመቻ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጽዳት ዙሪያ እያከናወኗቸው ያሉ ተግባራት ኤጀንሲው ለሚያከናውናቸው ስራዎችና ህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ትልቅ አስተዋጾ እያበረከቱ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በ2010 ዓ.ም 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ህዝብ በጽዳቱ ላይ መሳተፉን አስታውሰው በ2011 ዓ.ም ደግሞ 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ህዝብ በተለያየ ጊዜ በተደረጉ የጽዳት ዘመቻዎች መሳተፋቸውን ጠቁመዋል።

በዚህም ከፍተኛ ለውጦች ቢስተዋሉም አሁንም የሚፈለገው ደረጃ ላይ አለመደረሱን አስረድተዋል።

እንደ ዋና ስራ አስኪያጁ ገለጻ ፤ አዲስ አበባን ንጹህና አረንጓዴ ማድረግ ከተፈለገ ከተማዋን የማጽዳት ስራውን በማጠናከር የቆሻሻ አያያዝ ጉድለቶችን በዘላቂነት ለመፍታት መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

መላውን ህብረተሰብ በማሳተፍ በሚካሄድ የጽዳት ዘመቻ የአዲስ አበባን ጽዳት በሚፈለገው ደረጃ ከፍ እንዲል ማድረግ እንደሚቻል አቶ እሸቱ ገልጸዋል።

ኤጀንሲው 140 ለሚሆኑ የተቋሙ ሰራተኞች ቀደም ብሎ ስልጠና በመስጠት በ 2011 የክረምት የማጠናከሪያ ትምህርት የሚወስዱ 60 ሺህ ተማሪዎች በቆሻሻ አወጋገድ ላይ ስልጠና እንዲያገኙ ማድረጉንም አመልክተዋል።

መልካም አስተሳሰብን ለመስበክ የሚያግዝ የጽዳት ዘመቻ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በሚያዚያ ወር ላይ መካሄዱ ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የጽዳት ዘመቻው ቆሻሻን ከአካባቢ መጥረግ እንደሚገባ ሁሉ ከአእምሮም መጥፎና ክፉ ኃሳብን በመጥረግ በመልካም አስተሳሳብ መተካት እንደሚገባ ለማስተማር ጭምር እንደሆነ ከዚህ ቀደም መናገራቸው ይታወቃል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጠነሰሰው አገር አቀፍ የጽዳት ዘመቻ ”አካባቢያችንን ከቆሻሻ፣ ውስጣችንን ከቂምና ከጥላቻ እናጽዳ” በሚል መሪ ሃሳብ ባለፉት ጊዜያት መከናወናቸው ይታወሳል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልእክት “ከተማን ማፅዳት ቤትንና ራስን ማፅዳት እንደሆነ ሁላችን ተረድተን ከተማችንን ውብና ማራኪ በማድረግ ፅዳትን ባህላችን እናደርጋለን” ብለዋል፡፡