ሴቶች የተሳተፉበት የዜግነት አገልግሎት በቶኬ ኩታዬ ወረዳ በችግኝ ተከላ ተጀመረ

70
አምቦ ኢዜአ ነሐሴ 10/2011 በምዕራብ ሸዋ ዞን በጎ ፈቃደኛ ሴቶች የተሳተፉበት የዜግነት አገልግሎት ስራ ዛሬ በቶኬ ኩታዬ ወረዳ በችግኝ ተከላ ተጀመረ፡፡ በፕሮግራሙ መክፈቻ ስነስስርዓት ወቅት የዞኑ ሴቶችና ወጣቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ጸሐይ ኃይሉ እንዳሉት በሴቶች ተሳትፎ የሚካሄደው የዜግነት አገልግሎት የችግኝ ተከላ፣ የደም ልገሳ፣ እና ለሴት ተማሪዎች የትምህርት መገልገያ ቁሳቁስ ድጋፍ ላይ ያተኩራል። ዛሬ በተጀመረው ፕሮግራሙ የዞንና ወረዳ ሴቶች ተሳትፈው በቶኬ ኩታዬ ወረዳ ኖራ ፋብሪካ አካባቢ ከአራት ሺህ በላይ ችግኞች ተክለዋል፡፡ በተጨማሪም ለችግረኛ ሴት ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁሶችና የጫማ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡ አምቦ ከተማ ሴቶችና ወጣቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ታደለች አለማየሁ በበኩላቸው የከተማው ሴቶች ዛሬ 1ሺህ 116 ችግኞችን መትከላቸውን ገልጸዋል። በአገልግሎቱ እየተሳተፉ ካሉት ውስጥ ወይዘሮ አበባ መንግስቱ በሰጡት አስተያየት የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት የዜግነት ድርሻቸውን ለመወጣት ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። የተቸገሩትን በገንዘብ፣ በጉልበትና በእውቀት በመደገፍ የሚጠበቅባቸውን እንደሚያደርጉ የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ብርሃኔ ድርርሳ የተባሉ የአገልግለቱ ተሳታፊ ናቸው፡፡ በምዕራብ ሸዋ ዞን በሚገኙ 22 ወረዳዎች  የዜግነት አገልግሎት ስራው ላይ ከ26ሺህ የሚበልጡ  በጎ ፈቃደኛ ሴቶች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል። የዞኑ ሴቶች የአረንጓዴ አሻራ ቀን የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ላይም የነቃ ተሳትፎ ማድረጋቸውም ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም