የመንግስታቱ ድርጅት በትሪፖሊ በህክምና ባለሙያዎች ላይ የተፈፀመውን ጥቃት አወገዘ

76

ኢዜአ ነሃሴ 10/2011 በትሪፖሊ በህክምና ባለሙያዎች እና የህክምና መሳሪያዎቻቸው ላይ የተፈፀመውን ጥቃት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማውገዙን በሊቢያ የመንግስታቱ ድርጅት ልዩ ልዑክ ጋሳን ሳላሜ መግለፃቸውን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል።

ከሚያዚያ ወር ጀምሮ የህክምና ባለሙያዎችና መገልገያ መሳሪያዎች ላይ ጥቃት የተፈፀመ ሲሆን በዚህም ሆስፒታሎችንና መሰል የመስክ ሆስፒታሎችን ጨምሮ በሲቪልና ወታደራዊ አምቡላንሶች ላይ ከ37 የሚልቁ ጥቃቶች መሰንዘራቸውን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሊቢያ ድጋፍ ሰጪ ተልዕኮ አመልክቷል፡፡

የጤና ባለሙያዎችን እና መገልገያ መሳሪያዎቻቸውን ኢላማ ያደረገው ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት “የጦር ወንጀል ነው” ሲሉ በሊቢያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ገሃሳን ሳላም ድርጊቱን ጠንከር ባለ ቃል ማውገዛቸውን በመረጃው ሰፍሯል፡፡

እንደ ዘገባው ከሚያዚያ ወር ጀምሮ የሃገሪቱን ዋና ከተማ ትሪፖሊን ለመቆጣጠር ከሚሞክረው ከተቃዋሚ ሃይል ጋር መንግስት ከባድ ፍልሚያ እያደረገ ይገኛል።

በዚሁ ውጊያ ሳቢያ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች ሲሞቱ ሌሎች ከ5,700 የሚልቁት ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል እንዲሁም ከ120,000 በላይ የሚሆኑት ንፁሃን ዜጎችም ቤት ንብረታቸውን ለቀው ተሰደዋል ሲል የአለም ጤና ድርጅት ሪፖርትን ዋቢ በማድረግ ሲ ጂ ቲ ኤን አመልክቷል፡፡

የቀድሞው የሃገሪቱ መሪ ሙአመር ጋዳፊ እ.አ.አ 2011 ከስልጣን ከተወገዱ ጀምሮ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመመስረት ትግል የሚያደርጉ ሃይሎች ሊቢያን ብጠብጥና አለመረጋጋት ውስጥ እንድትገባ ካደረጓትም ሰነባብተዋል በማለት ሲ ጂ ቲ ኤን ሂደቱን  አስታውሷል፡፡