በዞኑ በደረሱ የትራፊክ አደጋዎች በ19 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደረሰ

126
ደብረ ማርቆስ (ኢዜአ ) ነሀሴ 10 ቀን 2011- በምስራቅ ጎጃም ዞን ሁለት የተለያዩ አካባቢዎች በደረሱ የትራፊክ አደጋዎች በ19 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ። የመምሪያው የህዝብ ግንኙነት የሥራ ሂደት አስተባባሪ ኢንስፔክተር ጎበዜ ይርሳው ለኢዜአ እንደተናገሩት አደጋዎቹ ዛሬ የደረሱት በዞኑ ጎዛምን ወረዳ እና ደብረማርቆስ ከተማ ውስጥ ነው። በጎዛምን ወረዳ ወንቃ ቀበሌ አደጋው የደረሰው ከደብረማርቆስ ከተማ ወደ አማኑኤል ከተማ ይጓዝ የነበረና የሰሌዳ ቁጥሩ 1-37015 አ.ማ የሆነ ሚኒባስ መኪና በመገልበጡ ሲሆን በእዚህም በ13ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ነው የገለጹት። ተጎጂዎችን ወደ ደብረማርቆስ ሪፈራል ሆስፒታል በማምጣት የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል። ጉዳት ከደረሰባቸው ተሳፋሪዎች መካከልም ለሥራ ስምሪት የወጡ የትራፊክ ፖሊስ እና የመንገድ ትራንስፖርት ባለሙያ እንደሚገኙበት ጠቁመው የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑን አስረድተዋል። ዛሬ ጠዋት 4፡30 ላይ በደብረማርቆስ ከተማ ቀበሌ 04  በደረሰ የትራፊክ አደጋም በስድስት ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል። ተጎጂዎች በደብረማርቆስ ሪፈራል ሆስፒታል እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑንም ነው ኢኒስፔክተሩ የጠቆሙት። የአደጋው መንስኤ የሰሌዳ ቁጥር 3-06115 አ.ማ ሚኒባስ ተሽከርካሪ የሰሌዳ ቁጥሩ 3-06174 አ.ማ ከሆነ መለስተኛ የህዝብ ማመላለሻ መኪና ጋር በመጋጨቱ ምክንያት መሆኑንም አስረድተዋል። በሁለቱም አካባቢዎች በደረሰ የትራፊክ አደጋ ሰባት ሰዎች ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በቀሪዎች ላይ ቀላል ጉዳት መድረሱን ከኢንስፔክተር ጎበዜ ገለጻ ለማውቅ ተችሏል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም