አንጋፋው የኢኮኖሚ ባለሙያ አብደላ ሃምዶክ ለሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትርነት እጩ ሆኑ

66
ኢዜአ ነሐሴ 10 / 2011 የሱዳን የተቃዋሚዎች ጥምረት የቀድሞ የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑትን አብደላ ሃምዶክን ለሚቀጥሉት ሦስት የሽግግር ዓመታት የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ እጩ አድርጓቸዋል። አንጋፋው የኢኮኖሚ ባለሙያ ሃምዶክ በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ምክትል ፀሃፊነታቸው ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት መልቀቃቸው ይታወሳል።
ሚስተር ሃምዶክ ባለፈው ዓመት በቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሃሰን አል በሺር ለፋይናንስ ሚኒስትርነት ቢታጩም አለመቀበላቸው ተነግሯል። እጩው ጠቅላይ ሚኒስትር ለሱዳን እና ለህዝቧ መፃዒ ተስፋ ጠንክረው እንደሚሰሩ እናምናለን ሲል የሀገሪቱ የባለሙያዎች ማህበር ገልጿል። ሚስተር ሃምዶክ ከ30 ዓመታት በላይ በፖሊሲ ተንታኝነት፣ በኢኮኖሚ ባለሙያነት ሲያገለግሉ መቆየታቸውን ከተባበሩት መንግስታትየተገኘው የስራ ዳራቸው ያሳያል። ሱዳናውያን የኦማር ሃሰን አል በሺር አገዛዝ እንዲያበቃ በመቃወም ለወራት ሲያደርጉት የቆዩት ትግል አል በሺርን በወታደሩ ከስልጣን እንዲወርዱ አድርጓል። የሱዳን ወታደራዊ ምክር ቤት እና የነጻነትና የለውጥ ኃይሎች ጥምረት በመጪው ቅዳሜ የስልጣን ክፍፍል የመጨረሻ ስምምነት በመፈራረም የሦስቱን ዓመት የሽግግር ጊዜ ይጀምራሉ ተብሏል። ስድስት የሲቪል እና አምስት የወታደር በድምሩ 11 አባላት ያሉት ሉዓላዊ ምክር ቤት ተቋቁሞ የሽግግር ጊዜ ሂደቱን እንደሚከታተል ይጠበቃል። ምክር ቤቱ የሽግግር ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር እጩ ሆነው የቀረቡትን የሃምዶክን ሹመት ያጸድቃል ነው የተባለው። ቢቢሲ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም