ሰሜን ኮሪያ ከደቡብ ኮሪያጋር የሰላም ውይይት እንደማታደርግ አስታወቀች

76
ኢዜአ፤ ነሐሴ 10/2011 ሰሜን ኮሪያ “በደቡብ ኮሪያ የተሳሳቱ ድርጊቶች ምክንያት የሰላም ውይይት እንደማላደርግ ይታወቅልኝ” ብላለች። የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ሙን ጄ ኢን በትናንትናው ዕለት ስለ ውህደት መናገራቸውን ተከትሎ በሰጠችው የመልስ መግለጫ ነው ሰሜን ኮሪያ ውሳኔዋን ያስታወቀችው። ፕሬዚዳንት ሙን ጄ ኢን ኮሪያ ከጃፓን ነጻ የወጣችበትን ቀን ሲከበር ባደረጉት ንግግር፥ ሁለቱ ኮሪያዎች በፈረንጆቹ 2045 ይዋሃዳሉ ብለው ነበር። ከራሱ አልፎ ለምስራቅ እስያ እና ለዓለም የሚተርፍ ሰላማዊ እና የብልጽግና ቀጠና የሆነ  አንድ የኮሪያ ልሳነ ምድር እውን ይሆናል ሲሉም ተደምጠዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ፒዮንግያንግ ዛሬ ማለዳ ሁለት ሚሳኤሎችን ወደ ባህር ዳርቻ ማስወንጨፏን የደቡብ ኮሪያ ጦር አስታውቋል። ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ስድስት የሚሳኤል ሙከራዎችም አድርጋለች። በስያሜ ደረጃ ያልታወቁት የዛሬው የሙከራ አካል የሆኑት ሚሳኤሎች 230 ኪሎ ሜትር ርዝመት በ30 ኪሎ ሜትር ከፍታ ላይ መወንጨፋቸውም ተነግሯል። ሰሜን ኮሪያ ወደ ሚሳኤል ማስወንጨፍ ድርጊቷ የተመለሰችው አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ጥምር ወታደራዊ ልምምድ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው። የኮሪያ ልሳነ ምድር ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ተከትሎ ሰሜንና ደቡብ በሚል ለሁለት መሰንጠቁ ይታወሳል። ልሳነ ምድሩን ከኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ነጻ ለማድረግ በሰሜንና ደበብ ኮሪያዎች የተጀመረው ውይይት ሰሞኑን በውጥረት ውስጥ ይገኛል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም