በአገሮች መካከል ያለው ድንበር የትብብር እንጂ የልዩነት መንስኤ ሊሆን አይገባም – የኬንያው ምክትል ፕሬዚዳንት

140

“በምስራቅ አፍሪካ አገሮች መካከል ያለው ድንበር የትብብር እንጂ የልዩነት መንስኤ ሊሆን አይችልም” ሲሉ የኬንያው ምክትል ፕሬዚደንት ዊሊያም ሳሜሩቶ ተናገሩ።

ኢትዮጵያን ጨምሮ የአራት አገሮች የድንበር ተሻጋሪ ህዝቦች ተሳታፊ የሆኑበት የባህልና የቱሪዝም ፌስቲቫል በኬንያዋ ቱርካና ዋና ከተማ ሎድዋር እየተካሄደ ይገኛል።

በፌስቲቫሉ ላይ የኬንያው ምክትል ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሳሜሩቶ እንዳሉት በምስራቅ አፍሪካ አገሮች መካከል ያለው ድንበር  ግንብ ሳይሆን የትብብር ድልድይ ሊሆን ይገባል።

“በአገሮቻችን መካከል ያለው ድንበር ፖለቲካዊና ሰው ሰራሽ በመሆኑ የልዩነት መንስኤ ሊሆን አይገባም” ሲሉም አክለዋል።

አገራቱ ድንበሮቻቸውን ክፍት በማድረግ በህዝቦች መካከል የትብብር፣ በጋራ የመስራትና የሰላም ልምድ እንዲዳብር ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ምክትል ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል።

ኬንያ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት በማጠናከር በይበልጥ በንግድ መተሳሰር እንደምትፈልግም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን የልኡካን ቡድን የወከሉት በኬንያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለሰ አለም በበኩላቸው እንዳሉት ኢትዮጵያ ከሌሎች አጎራባች አገሮች ጋር የትብበር መንፈስ የማዳበርና በጋራ የመስራት ፍላጎት አላት።

ጎረቤት አገራት ህዝቦች በተለይም የኬንያ ቱርካና፣ የዩጋንዳ ካኦሞዞ፣ የደቡብ ሱዳን ኔቶፖሳ ህዝቦች ከኢትዮጵያ ጋር ከሚለዩባቸው ይልቅ አንድ የሚያደርጓቸው ጉዳዮች እንደሚበዙ አምባሳደሩ ተናግረዋል።

ይህም ወዳጅነት ይበልጥ እንዲጠናከር መንግስታት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

በስነ-ስርአቱ ላይ ከደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች የተውጣጡ 40 የባህል ቡድን አባላት ተሳትፈዋል፤ የአገሪቱን የተለያዩ የባህል ትርኢትም አቅርበዋል።

በኬንያ ቱርካ እየተካሄደ የሚገኘው የባህልና የቱሪዝም ፌስቲቫል ለአምስተኛ ጊዜ ሲሆን በቀጣይ ኢትዮጵያ ውስጥ ለማካሄድ ፍላጎት መኖሩ ተገልጿል።

በተለያዩ የኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ የሚኖሩ ህዝቦች ከሚጎራበቷቸው የተለያዩ አገራት ጋር በቋንቋ፣ በባህል፣ በስነ-ልቦና የህይወት ዘዬ በእጅጉ የተቆራኙ ህዝቦች ናቸው።