ኢሳት በአገር ቤት የገባበትን አንደኛ ዓመት ለማክበርና የ10 ዓመታት ጉዞውን የሚፈትሽ መድረክ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ያካሂዳል

123
ነሐሴ 9/2011 የኢትዮጵያ ሳተላይት ሬዲዮና ቴሌቪዥን (ኢሳት) ወደ አገር ውስጥ የገባበትን አንደኛ ዓመትና ከምስረታው ጀምሮ ያለውን የ10 ዓመታት ጉዞ የሚዳስስ መድረክ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሊያካሂድ መሆኑን አስታወቀ።
ድርጅቱ ዛሬ በአዲስ አበባ በሚገመኘው ስቱዲዮው በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በመጭው አዲስ ዓመት ተደራሽነቱን ይበልጥ በማስፋት በአገራዊ አንድነትና መግባባት ላይ እንደሚሰራ ገልጿል። ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት በኢትዮጵያ የኢሳት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሳባ አታሮና ከኢሳት ለንደን የመጣው ጋዜጠኛ ወንድማገኝ ጋሹ ናቸው። ኢሳት ተቀማጭነቱን በውጭ አገሮች በማድረግ ለስምንት ዓመታት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት እንዲከበር፣ አገራዊ አንድነት እንዲጠናከር፣ ኢትዮጵያዊያን እንዲቀራረቡ በነጻ ሚዲያ ተምሳሌትነት የህዝብ ዐይንና ጆሮ ሆኖ ሲያገለግል የነበረ ሚዲያ እንደነበር ገልጸዋል። ሚዲያው በዋሽንግተን፣ አምስተርዳምና ለንደን ስቱዲዮ ማዕከላት ሲሰራ እንደነበር ገልጸው፤ ባለፈው አንድ ዓመት በኢትዮጵያ የተፈጠረውን አገራዊ የፖለቲካ ምቹ ሁኔታ ተከትሎ አዲስ አበባ መግባቱን ኃላፊዎቹ አስታውሰዋል። በዚህም በአገር ቤት የነበረውን የአንድ ዓመት ጉዞ ለማክበርና ከተመሰረተ ጀምሮ ያለፈበትን የ10 ዓመታት ጉዞ የሚዳስስ መድረክ በመጭው አዲሱ ዓመት ዋዜማ ጳጉሜ 3 ቀን 2011 ዓ.ም ማዘጋጀቱን አቶ ወንድማገኝ አስታውቀዋል። 'የህዝብ ዐይንና ጆሮ በመሆን ሲያገለግል ነበር' ያሉት ድርጅታቸው፤ ወደፊትም ተደራሽነቱን ይበልጥ በማስፋት አገራዊ አንድነትና መግባባት ላይ በማተኮር የሚዲያና ጋዜጠኝነት መርህን የተከተለ ህዝባዊ ወገንተኛ ሚዲያ ሆኖ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። ኢሳት በአዲስ አበባ የሚገኘውን ስቱዲዮው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከማሟላት ባሻገር ብቃትና ክህሎት ያላቸውን ሙያተኞች በመቅጠር ነጻና ገለልተኛ ሚዲያ ሆኖ እንደሚሰራ ተናግረዋል። ለዓመታት ከህዝብ በሚሰበሰብ ገቢ ሲመራ እንደነበር የተነገረለት ኢሳት እንደማንኛውም የንግድ ድርጅት የገቢ ምንጮችን ለማሳደግ አቅዶ እየሰራ መሆኑን ኢንጂነር ሳባ ገልጸዋል። "በዚህም ጥሩ ተስፋ አለን" ያሉት ኢጂነር ሳባ በቅርቡ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና የግል ተቋማት ምርትና አገልግሎታቸውን ለማስተዋወቅ ኢሳትን እንደሚጠቀሙ ስራ አስኪያጇ ይፋ አድርገዋል። ''ኢሳት በንግድ ወይም አትራፊ ድርጅትነት ከተመራና በስፖንሰር አድራጊዎች ገቢ ከተንቀሳቀሰ የሚዲያው ባለቤቱና የቀጣይ ድርጅታዊ አወቃቅሩ እንዴት ይሆናል'' ለሚለው ጥያቄ ግን ግልጽ ምላሽ አልተሰጠበትም። ከመንግስትና ግል ድርጅቶች በሚያገኘው ገቢ የገቢ ምንጩን ለማሳደግ እንደሚሰራ መጀመሪያ ላይ ቢገልጹም ኢሳት ከዚህ በፊት እንደነበረው 'አትራፊ ያልሆነ ድርጅት' ሆኖ እንደሚቀጥል ምላሽ ሰጥተዋል። በድርጅታዊ አወቃቅርና ባለቤትነት ጉዳይ ኢሳት የአክሲዮን፣ ህዝባዊ ሚዲያ ወይስ የፖለቲካ ድርጅት ሆኖ ይቀጥላል በሚል ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄ ጉዳዩ ላይ ከዚህ በፊት ተገልጿል በሚል ግልጽ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል። በኢንተርኮንቲኔንታል በሚደረገው በኢሳት ዝግጅት ከ2 ሺህ 500 በላይ እንግዶች ይሳተፋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ታዋቂ ሰዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ይታደማሉ ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም