አስር ሚሊዮን ሴቶች የሚሳተፉበት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ነገ በመላው ኦሮሚያ ይጀመራል

90
ነሐሴ 9/2011 በኦሮሚያ ክልል አስር ሚሊዮን ሴቶች የሚሳተፉበት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ነገ ነሐሴ 10 ቀን 2011 ዓም እንደሚጀመር የክልሉ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ። የኦሮሚያ ክልል ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሙና አህመድ እና የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዲፒ) የሴቶች ሊግ ኃላፊ ወይዘሮ ሰዓዳ ኡስማን በመርሃ ግብሩ ዙሪያ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል። የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ በችግኝ ተካለ፣ በደም ልገሳ፣ በአካባቢ ጽዳት እና ለሴት ተማሪዎች የትምህርት መገልገያ ቁሳቁስ ድጋፍ በማቅረብ ላይ ያተኩራል ተብሏል። በዚህም መሰረት በመላው ኦሮሚያ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በበጎ ፈቃደኞቹ ሴቶች ይተከላል ተብሎ ይጠበቃል። በበጎ ፍቃድ አገልግሎት መርሃ ግብሩ ከ25 ሺህ በላይ ለሚሆኑና የገንዘብ አቅመ የሌላቸው ሴት ተማሪዎች የትምህርት መገልገያና የግል ንህጽና መጠበቂያ ቁሳቁስ እንደሚሰጥ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ ሙና አህመድ ተናግረዋል። የጨፌ ኦሮሚያ በቅርቡ ባወጣው የዜግነት አገልግሎት ደምብ መሰረት የተለያዩ በጎ ፍቃድ አገልግሎት ሥራዎች በመላው ኦሮሚያ በመከናወን ላይ ይገኛል ሲሉ የኦዲፒ ሴቶች ሊግ ኃላፊ ወይዘሮ ሰዓዳ ኡስማን ገልፀዋል። ነገ የሚጀመረውና ሴቶችን ብቻ የሚያሳትፈው በጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሳካ ዘንድ መላው የክልሉ ሴት በንቃት እንዲሳተፍ ወይዘሮ ሰዓዳ ጥሪ አቅርበዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም